እነዚህ ማህበራዊ ሚድያ ላይ የተሰራጩ የተሽከርካሪዎች ምስሎች ምን ያሳያሉ?

በሱዳን ዳርፉር ግዛት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የአፍሪካ ህብረት በጋራ የሚያካሂዱት የሰላም ማስከበር ተልእኮ ላይ ሲሰሩ የነበሩ መኪኖች እንደሆኑ የሚያሳይ UNAMID የሚል ፅሁፍ ከጎናቸው የተጻፈባቸው በርከት ያሉ ከባድና ቀላል መኪኖች በሰልፍ ሲገቡ የሚያሳይ ቪድዮ በማህበራዊ ሚዲያ አውታሮች ሲዘዋወር ተመልክተናል።

እነዚህ መኪኖች በቅርቡ ከዳርፉር የሰላም ማስከበሩን ተልእኮ የጨረሰው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል መሆናቸውን በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ይፋዊ የትዊተር ገፅ አስታውቋል።

“የምድር ጦራችን በዳርፉር ለማገልገል ሲጠቀምባቸው የነበሩት እነዚህ መኪኖች የኢትዮጵያ መንግስት ንብረቶች ናቸው” ያለው ኤምባሲው እነዚህ መኪኖች ለኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት አገልግሎታቸውን እንዲሰጡ ተደርገው ይዘጋጃሉም ብሏል።

በዳርፉር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የአፍሪካ ህብረት የሰላም ማስከበር የጋራ ተልእኮ UNAMID (UN-African Union Mission in Darfur) ከ13 ዓመታት የሰላም ማስከበር ተልእኮው በኋላ ከሚቀጥለው ዓመት ሰኔ ወር በፊት ከዳርፉር ጠቅልሎ ለመውጣት እቅድ እንደተያዘለትም ለማወቅ ተችሏል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::