በቀይ መስቀል ቁሳቁሶች ውስጥ የሚታዩት ፍላሽ ዲስኮች ምንድን ናቸው? 

ሰሞኑን ወደ ትግራይ ክልል ያመሩ በነበሩ የአለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ተሽከርካሪዎች ላይ በአፋር ክልል በተደረገ ፍተሻ በርከት ያለ ጥሬ ገንዘብ ስለመያዙ የሚገልጹ መረጃዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ተሰራጭተዋል። 

ይህንን ተከትሎም ኮሚቴው ዛሬ ባወጣው መግለጫ በምስሉ ላይ የሚታዩት ቁሳቁሶች በሙሉ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታና የህክምና ቁሶችንም ያካትታል፣ የሚመለከታቸው የፌደራልና የክልል መንግስት አካላት በቅድሚያ እንዲያውቋቸው ተደርገውና ፈቃድ ተገኝቶባቸው የተጓጓዙ ናቸው ብሏል። 

ይህን ተከትሎ ማህበራዊ ሚድያ ላይ የተሰራጨው ምስል ላይ የሚታዩት ፍላሽ ዲስኮች ምን እንደሆኑ ብዙዎችን ማነጋገር ቀጥለዋል። በዚህ ዙርያ ኢትዮጵያ ቼክ አዲስ አበባ የሚገኘውን የቀይ መስቀል ኮሚቴ የኮሚኒኬሽን ክፍል ተጨማሪ መረጃ ጠይቋል። 

“ቀይ መስቀል ለእርዳታ ማስተባበር በብዛት በሚጠቀምበት መኪና ቅርፅ የተሰራ የማስተዋወቂያ (promotional material) ፍላሽ ዲስክ ነዉ፣ ሌላ ምንም ነገር አይደለም። ጃንጥላ፣ የቁልፍ መያዣ፣ የጠረጴዛ ሰአት… ወዘተ እንደሚዘጋጀዉ ለፕሮሞሽን የተዘጋጀ ነው። በሁሉም ስፍራ እንደምናረገው ቢሯችን ለሚመጡ ሰዎች በስጦታ የሚሰጥ ነው፣ ውስጡም ባዶ እንደሆነ ተፈትሾ የተረጋገጠ ነው” የሚል መልስ ከኮሜቴው አግኝተናል።  

ኢትዮጵያ ቼክ በቁሳቁሶቹ ጉዞ ዙርያ ባደረገው ተጨማሪ ማጣራት ቀይ መስቀል ኮሚቴው ከአፋር ክልላዊ መንግስት፣ ከአደጋ መከላከል እና ዝግጁነት እንዲሁም ከፌደራል የፀጥታ አካላት እውቅና ተሰጥቶት እንደነበር ማረጋገጫ አግኝቷል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::