ከሰሞኑ በአማራ ባንክ ስም የተከፈቱ በርከት ያሉ የፌስቡክ ገፆችና ቴሌግራም ቻናሎች የተለያዩ መልክቶችን ሲያስተላልፉ ተመልክተናል!

በባንኩ ስም ከተከፈቱ የቴሌግራም ቻናሎች መካከል አንዱ ከ38 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት ሲሆን ባንኩ ሥራ መጀመሪያ ፕሮግራሙን እንዲሁም አዲሱን አመት ምክንያት በማድረግ እስከ መስከረም 05, 2014 ድረስ የሚቆይ ልዩ የሽልማት ፕሮግራም ማዘጋጀቱን ጽፏል።

ከሽልማቶቹ መካከልም ለ200 እድለኞች ከ300,000 ብር በላይ ዋጋ የሚያወጡ ባለ 3 እግር ተሽከርካሪዎችና ሌሎች ሽልማቶች እንደተዘጋጁ ይናገራል።

ይህን ጉዳይ ለማጣራት ኢትዮጵያ ቼክ ከባንኩ መስራቾች ለአንዱ በመደወል መረጃዎችን ጠይቋል።

ስማቸዉ እንዳይጠቀስ የጠየቁት የባንኩ መስራች አማራ ባንክ ምንም አይነት የማህበራዊ ሚዲያ ገፅ እንደሌለዉ ነግረዉናል።

“ለጊዜዉ በምስረታ ላይ ስለሆነ ኦፊሺያል ገፅ የለንም። ፌስቡክም፤ ቴሌግራምም ምንም አይነት በማህበራዊ ሚዲያ ገፅ የለንም” ብለዋል።

ገና በምስረታ ላይ ያለ ባንክ እንደዚህ አይነት የሽልማት እድሎችን ያዘጋጃል ብሎ መገመት እንደሚያስቸግር፤ ስለዚህም የሽልማት ማስታወቂያዉ የባንኩ እንዳልሆነም ተናግረዋል።

እስከ አሁን ድረስ የባንኩን ማስታወቂያዎች በቴሌቭዥ፤ ሬድዮና ጋዜጣ ሲያስተላልፉ እንደነበርና በማህበራዊ ሚዲያ ግን የተለያዩ ግለሰቦች በግለሰብ ደረጃ ባንኩን ሲያስተዋውቁ መቆየታቸዉን እኝህ የአማራ ባንክ መስራች ለኢትዮጵያ ቼክ ነግረዋል።

በመጨረሻም የባንኩ ምስረታ እየተጠናቀቀ በመሆኑ ባንኩ በቅርብ ጊዜ የራሱን የተረጋገጡ /Verified/ ማህበራዊ ሚዲያ ገፆች እንደሚኖረዉ ነግረዉናል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::