ይህ የሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም የፌስቡክ ገፅ አይደለም!

ከ9,900 በላይ ተከታዮች ያሉትና በሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዷለም ስምና ፎቶ በመጠቀም የተከፈተ የፌስቡክ ገጽ መኖሩን ተመልክተናል።

“ብናልፍ አንዷለም – Binalf Andualem Official” የሚል ስያሜ ያለው ይህ ገጽ የተለያዩ መልዕክቶችን የሚለጥፍ ሲሆን በርከት ያሉ ሰዎች የመልዕክቶችን የስክሪን ቅጅ (screenshots) በትዊተርና በፌስቡክ አካውንቶቻቸው ሲያጋሩም አስተውለናል።

ገፁ በትናንትናው እለትም ” ዘማቾችን በተመለከተ” የሚል በምስሉ ላይ የሚታየውን አነጋጋሪ ፅሁፍ አጋርቶ ብዙዎችን ግራ እያጋባ ይገኛል።

በፌስቡክ የገጽ ግልጽነት (Page Transparency) አገልግሎት እንደተመለከትነው ይህ የፌስቡክ ገጽ በታህሳስ ወር 2013 ዓ.ም የተከፈተ ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሁለት ግለሰቦች ይቆጣጠሩታል።

ኢትዮጵያ ቼክ የገጹን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ አቶ ብናልፍ አንዷለምን የጠየቀ ሲሆን ገጹ የእርሳቸው አለመሆኑን አስታውቀዋል። ገፁ የርሳቸው እንዳልሆነ ከሁለት ሳምንት በፊት ኢትዮጵያ ቼክ መረጃ አጋርቶ ነበር። አቶ ብናልፍ ምንም አይነት የፌስቡክ አካውንት እንደሌላቸውም ጨምረው ገልጸዋል።

ትክክለኛ የማህበራዊ ሚዲያ አካውንቶችንና ገጾችን በመከተል እራስዎን ከተዛቡ እና ሀሠተኛ ከሆኑ መረጃዎች ያርቁ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::