ይህ ኢትዮጵያውያን የቴክኖሎጂ አበልጻጊዎች እስከ 2.5 ሚሊየን ዶላር መሸለማቸውን የሚገልፅ መረጃ የተሳሳተ ነው!

ከሁለት ቀን በፊት ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እና የኢትዮጵያ ፕረስ ድርጅት የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን ዋቢ በማድረግ “በዓለም አቀፍ ውድድሮች ተወዳድረው በማሸነፍ እስከ 2.5 ሚሊየን ዶላር ያገኙ ወጣት የቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለሙያዎች እውቅናና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል” በሚል የቀረበ ዜና ነበር። 

በመረጃው መሰረት አበልፃጊዎቹ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ተወዳድረው በማሸነፍ ከ25 ሺህ ዶላር እስከ 2.5 ሚሊየን ዶላር ሽልማት አግኝተዋል የተባለ ሲሆን በሀገር ውስጥ ከ200 በላይ የስራ እድሎች እንዲሁም ከ100 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር  ሀብት አግኝተዋል። 

ኢትዮጵያ ቼክ በዚህ ዙርያ የደረሰውን ጥቆማ ተከትሎ ባደረገው ማጣራት ሽልማቱ የተጠቀሰው መጠን እንዳልሆነ እና እጅግ ተጋኖ እንደቀረበ ማረጋገጥ ችሏል። 

ትክክለኛው መረጃ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከኮርያ አለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ባገኘው ድጋፍ በአንደኛ ዙር ለተካፈሉ እና አንደኛ ለወጡ 3,000 ዶላር፣ ሁለተኛ ለወጡ 1,500 ዶላር እንዲሁም ሶስተኛ ለወጡ 1,000 ዶላር አበርክቷል። 

በዚህም መሰረት “እስከ 2.5 ሚሊየን ዶላር” ሽልማት እንደተበረከተ የቀረበው መረጃ የተሳሳተ ነው። በዚህ ዙርያ ኢትዮጵያ ቼክ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሀላፊ መረጃ የጠየቀ ሲሆን “ይህ ስህተት መሆን አለበት” የሚል አጭር መልስ አግኝቷል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::