“በጅማ አየር ማረፍያ የተከሰተ ምንም አይነት ችግር አልነበረም፣ ዛሬም በረራዎች እየተስተናገዱ ነው”— የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ እስክንድር አለሙ ለኢትዮጵያ ቼክ

ትናንት ምሽት የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በጅማ አባጅፋር አውሮፕላን ማረፊያ በደረሱ ፍንዳታዎች የሰዎች ህይወት ማለፉን እንዲሁም ጉዳት መድረሱን አስነብበዋል። በተጨማሪም ፍንዳታውን ተከትሎ የአውሮፕላን ማረፊያው ስራ ማቆሙን እና ወደ ጅማ የሚደረጉ በረራዎች መቋረጣቸውን ጽፈዋል።

ጉዳዩን በተመለከተ የጅማ ዞን ኮሚኒኬሽን መምሪያና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬ በፌስቡክ ገጾቻቸው መግለጫ የሰጡ ሲሆን የተሰራጨው መረጃ ሀሠተኛ መሆኑን አስታውቀዋል።

የጅማ ዞን ኮሚኒኬሽን መምሪያ መረጃው ሀሠተኛ መሆኑን ገልጾ የአሮፕላን ማረፊያውንና ሠራተኞችን የሚያሳዩ ፎቶዎችን አያይዞ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበኩሉ የመረጃውን ሀሠተኛነት የገለጸ ሲሆን “በአሁኑ ሰዓት በጅማ መደበኛ የኤርፖርት እና የበረራ ስራዎቻችን በተለመደው መልኩ እየተከናወኑ ይገኛሉ” ብሏል።

ኢትዮጵያ ቼክ የትናንት Flight Radar የበረራ መረጃዎችን የተመለከተ ሲሆን ቢያንስ አንድ በረራ ተሰርዞ እንደነበር ያመለክታል።

በዚህ ዙርያ ኢትዮጵያ ቼክ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑትን አቶ እስክንድር አለሙን አናግሯል። በረራ የሚሰረዘው መንገደኛ ሳይኖሩ ሲቀር መሆኑን አብራርተው ይህም በጣም የተለመደ መሆኑን ተናግረዋል።

“በጅማ አየር ማረፍያ የተከሰተ ምንም አይነት ችግር አልነበረም፣ ዛሬም በረራዎች እየተስተናገዱ ነው” ብለዋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::