“መጪው አፍሪካ ዋንጫ ይራዘማል ወይም ይሰረዛል የሚለው ወሬ የሀሰት ነው”— የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ሉክስ ሴፕቴምበር

በርካታ አለም አቀፍ ሚድያዎች፣ የስፖርት ቻናሎች እና የስፖርት ተንታኞች ካሜሮን የምታዘጋጀው እና ኢትዮጵያ የምትሳተፍበት የ2022 የአፍሪካ ዋንጫ እንደተሰረዘ ወይም ሊራዘም እንደሆነ ሰሞኑን ዘግበዋል።

ይህን ተከትሎ በርካታ የሀገር ውስጥ የስፖርት መረጃ ምንጮችም ይህን አስተጋብተዋል።

ለዚህ መራዘም እንደ ምክንያትነት የቀረበው “የተጫዋቾች ጤንነት” እንደሆነ የተነገረ ሲሆን ይህም በአፍሪካ ያለው የኮቪድ ሁኔታ በተለይ በቅርብ ግዜያት ከኦሚክሮን ዝርያ መከሰት ጋር ይያያዛል ተብሎ ነበር። አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን በጉዳዩ ዙርያ በቅርቡ ውሳኔ ላይ ይደርሳል።

ይሁንና የኮንፌዴሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ሉክስ ሴፕቴምበር ውድድሩ ይራዘማል እና ይሰረዛል የሚለውን መረጃ “የሀሰት ዜና” ብሎታል።

በተጨማሪም ከውድድሩ ቀደም ብለው ካሜሮን የገቡት የኮንፌዴሬሽኑ ዋና ፀሀፊ ቬሮን ሞሴንጎ-ኦምባ ውድድሩ በእርግጥ ይካሄዳል ብለው ማረጋገጫ ሰጥተዋል። አክለውም “ባለፉት ጥቂት ወራት አጥጋቢ የሚባል ዝግጅት አድርገናል” ያሉ ሲሆን ተወዳዳሪዎችን እና እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት እንደተጠናቀቀ አሳውቀዋል።

የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር እ.አ.አ ጃንዋሪ 9 በካሜሮን መካሄድ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፣ ከተራዘመ ግን ቀጣዩ ውድድር ከሁለት አመት በሗላ በኮትዲቯር ይካሄዳል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::