“ይህ በእኔ ስም እና ምስል ተከፍቶ ገንዘብ እናሰባስብ የሚለው የፌስቡክ ገፅ ሀሰተኛ ነው፣ የኔ አይደለም”— አትሌት ሀይሌ ገ/ስላሴ ለኢትዮጵያ ቼክ

ከትናንት በስቲያ ሰኞ እለት በአትሌት ሀይሌ ገ/ስላሴ ስም እና ምስል የተከፈተ በምስሉ ላይ የሚታየው የፌስቡክ አካውንት የበርካቶች ጥያቄ ሆኗል። ገፁ በሁለት ቀን ብቻ 32,000 ተከታይ ያገኘ ሲሆን አሁንም ቁጥሩ እየጨመረ እንደሆነ ተመልክተናል።

በገፁ ላይ “የፌስቡክ አካውንቴን አዲሱን እያስተዋወኩ እንደሆነ ይታወቃል ይህ ከዚ በሆላ የምጠቀምበት ትክክለኛው አካውንቴ እንደሆነ አውቃቹህ ለሁሉ ኢትዮጵያዊ እንዲደርስ ዘንድ በማረግ የየድርሻቹህን አግዙኝ ስላገዛቹህኝ አመሰግናለሁ” በሚል ትናንት የቀረበው ፅሁፍ ብቻ ከ570 ግዜ በላይ ሼር ተደርጓል፣ ይህም ብዙ ሰው ገፁን እንዲቀላቀል አንዱ ምክንያት ሆኗል።

ገፁ እንደገና ትናንት “በጦርነትቱ ለተጎዱ ትምህርት ቤቶች ገንዘብ እናሰባስብ፣ ለ1ላይክ 300 ብር፣ ለ1 ኮሜንት 200 ብር፣ ለ 1ሼር 500 ብር… ለመስጠት ቃል እገባለሁ ለ 48 ሰአት ብቻ የሚቆይ” የሚል መልዕክት አስፍሮ አሁን ላይ ከ17 ሺህ በላይ ሪአክሽን፣ 6,500 ኮመንት እንዲሁም 8 ሺህ ግዜ ተጋርቷል።

በዚህ ዙርያ ኢትዮጵያ ቼክ አትሌት ሀይሌ ገ/ስላሴን ዛሬ አናግሯል። አትሌት ሀይሌ ይህ ገፅ የእርሱ እንዳልሆነ እና የሚተላለፈው መልዕክትም እርሱን እንደማይወክል ተናግሯል።

“የዛሬ አምስት አመት ገደማ የተከፈተ እና በፌስቡክ ቬሪፋይድ የሆነ አካውንት አለኝ (https://www.facebook.com/HaileGebres)፣ ይህም እንዳይከፈት ፈልጌ ነበር ግን በስምህ መከፈቱ ስለማይቀር ሰው እንዳይሳሳት ተብሎ ተከፍቷል። ይሁንና እሱንም አልጠቀምበትም፣ ሌላም የፌስቡክ አካውንት የለኝም” በማለት አትሌት ሀይሌ ለኢትዮጵያ ቼክ ተናግሯል።

አትሌት ሀይሌ ትዊተር ላይም ቬሪፋይድ አካውንት እንዳለው የጠቀሰ ሲሆን (https://twitter.com/HaileGebr?t=ykGNWKzMPUvIhhr4XdY9sw&s=09) እሱም ማናጀሮቹ በሆኑት የ Global Sports ድርጅት አልፎ አልፎ መልዕክቶች እንደሚሰራጩበት ጠቁሟል።

ተመሳስለው ከሚከፈቱ ሀሰተኛ አካውንቶች ራሳችንን እንጠብቅ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::