የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ወደ ሼር ኩባንያነት እንደተቀየረ የሚያሳየው ማስታወቂያ የተሳሳተ ነው!

‘OKEthiopia.com’ የተባለና የሽያጭና የስራ ማስታወቂያዎችን እንዲሁም መረጃዎችን የሚያጋራ ድረ-ገጽ በትናንትናው ዕለት የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ያወጣውን ክፍት የስራ ማስታወቂያ ለጥፏል።

ማስታወቂያው በእንግሊዘኛ ቋንቋ የተላለፈ ሲሆን ድረ-ገጹ “Ethiopian Postal Service S.C Job Vacancy 2022 Ethiopia” በሚል ርዕስ ስር አጋርቷል። በተጨማሪም ከ41 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት “Ethiojobs ethiopianjob vacancy”
የተባለ የፌስቡክ ገጽ ይህንኑ ርዕስ በመጠቀም የስራ ማስታወቂያውን ለጥፏል።

ከላይ የተቀመጠውን ርዕስ የተመለከቱ የድርጅቱ ሰራተኞች የሆኑ የኢትዮጵያ ቼክ ተከታታዮች “የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት የመንግስት ተቋም መሆኑን ነው የምናውቀው። አሁን ቅርብ ባወጣው ክፍት የስራ ቦታ ማስታወቅያ ላይ Ethiopian Postal Service S.C ብለው ለጥፈዋል።ይሄ አንጋፋና ትልቅ ተቋም እንኳን መላው ህዝብ እኛ ሰራተኞቹ ራሱ ሳናቅ ተሽጦ ነው? ለምንድነው የሼር ኩባንያ ያሉት” የሚል ጥያቄ አድርሰውናል።

ኢትዮጵያ ቼክ ጉዳዩን በተመለከተ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅትን አነጋግሯል።

የድርጅቱ የሰው ሃብት አገልግሎት ከላይ የተጠቀሰውን ማስታወቂያ ለሪፖርተር ጋዜጣ መላኩን የገለጸ ሲሆን በተላከው ማስታወቂያ ላይ የድርጅቱ ትክክለኛ ስም ማለትም “የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት” ወይንም በእንግሊዘኛ “Ethiopian Postal Service Enterprise” መጠቀሙን አስታውቋል። ኦኬ ኢትዮጵያን ድረ-ገጽ የተጠቀመው ስምም የተሳሳተ መሆኑን ገልጿል።

ኢትዮጵያ ቼክ በሪፖርተር ጋዜጣ የወጣውን ክፍት የስራ ማስታወቂያም የተመለከተ ሲሆን “Ethiopian Postal Service Enterprise” የሚለውን ትክክለኛ ስም መጠቀሙን አረጋግጧል።

በተጨማሪም የድርጅቱን ማቋቋሚያ አዋጅ የተመለከትን ሲሆን የድርጅቱ ትክክለኛ ስም “የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት” ወይም በእንግሊዘኛ “Ethiopian Postal Service Enterprise” መሆኑን አረጋግጠናል።

ኢትዮጵያ ቼክ የተሳሳተ ስያሜን ያጋራውን ኦኬ ኢትዮጵያን ስለጉዳዩ የጠየቀ ሲሆን “በስህተት ሊሆን ይችላል፤ እንመለከተዋለን” የሚል ምላሽ አግኝቷል። ሆኖም ይህ ይህ መረጃ እስከተጻፈበት ሰዐት ድረስ አለመስተካከሉን ተመልክተናል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::