“የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዕጩ ኮሚሽነሮች ዝርዝር ይፋ አልተደረገም”— ኢትዮጵያ ቼክ ከህዝብ ተወካዮች ም/ቤ ያገኘው መረጃ

ከትላንት ጀምሮ “ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ውይይት አመቻች ኮሚሽን ኮሚሽነርነት አብላጫ ድምፅ ያገኙ እጩዎች” በሚል የ25 ሰዎችን ስም ዝርዝር ያካተተ ጽሁፍ በማህበራዊ ትስስር ገጾች እየተዘዋወረ ይገኛል።

ይህን መረጃ አንዳንድ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ተጠቃሚዎች በግል የማህበራዊ ትስስር ገጾቻቸዉ ከደረሷቸዉ ጥቆማዎች አብላጫ ድምጽ ያገኙ ዕጩዎች ዝርዝር እንደሆነ ጽፈዋል። ሌሎች ደግሞ ከኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የተገኘ መረጃ በማስመሰል እያጋሩት ይገኛል።

ይሁን እንጂ ይህ በማህበራዊ ትስስር ገጾች እየተዘዋወረ የሚገኘዉ “የ25 የዕጩ ኮሚሽነሮች” ስም ዝርዝር ትክክል እንዳልሆነ ኢትዮጵያ ቼክ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘዉ መረጃ ያመለክታል።

ስማቸዉ እንዳይጠቀስ የጠየቁት የኢትዮጵያ ቼክ ምንጭ የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዕጩ ኮሚሽነሮች ዝርዝር ይፋ እንዳልተደረገ፣ ከተደረገም በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ፌስቡክ ገጽ ይፋ እንደሚደረግ ነግረዉናል።

“የጥቆማ ጊዜ እራሱ ትላንት ነዉ ያበቃዉ” ያሉት ምንጫችን “ምክር ቤት ላይ ሳይጸድቅና እጩዎቹ ቃለመሃላ ሳይፈጽሙ ዝም ብሎ ይፋ አይደረግም” ብለዋል።

በኢትዮጵያ መግባባት ላይ ያልተደረሰባቸውና የሀገሪቱን ህልውና የሚፈታተኑ የተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ምክክር እንዲደረግ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ በህዘብ ተወካዮች ም/ቤት መጽደቁ ይታወሳል፡፡

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::