“በአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ ዙርያ የኔታ ትዩብ ላይ ሰሞኑን የቀረበው መረጃ የሀሰት ነው”— የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን 

የኔታ ትዩብ የተባለ የዩትዩብ ቻናል ከአንድ ቀን በፊት ሱዳን የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክን ጨፍጭፋ የኢትዮጵያን መሬት እያረሰች ነው የሚል በቃለ መጠይቅ ላይ የተመሰረተ መረጃ ይዞ ወጥቷል። ከዚህም በተጨማሪ የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ አዋሳኝ የሆነው የሱዳኑ ዲንደር ብሔራዊ ፓርክ በቅርብ ጊዜ በመስኖ የለማ አረንጓዴ ቦታ ስለመሆኑ በቃለ መጠይቁ ተገልጿል። 

ኢትዮጵያ ቼክ ይህን መረጃ ለማጣራት የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣንን አነጋግሯል። 

የባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ሰለሞን ወርቁ በየኔታ ትዩብ የተሰራጨው መረጃ ሀሠተኛ መሆኑ እና በፓርኩ ውስጥ ከእርሻም ሆነ ከጸጥታ ጋር የተገናኘ ችግር አለመፈጠሩን ተናግረዋል። የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ በሱዳን ከሚገኘው የዲንደር ብሔራዊ ፓርክ ጋር ኩታ ገጠም በመሆኑ ሁለቱ ፓርኮች በድንበር ተሻጋሪ የዱር እንስሳት ጥበቃ የጋራ ልማትና ጥበቃ እንደሚደረግላቸውም አቶ ሰለሞን ገልጸዋል። 

በዚሁ ቃለ መጠይቅ የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ አዋሳኝ የሆነው የዲንደር ብሔራዊ ፓርክ በቅርቡ በመስኖ የለማ ቦታ እንደሆነ የተገለጸውም የተሳሳተ መረጃ መሆኑን ኢትዮጵያ ቼክ ፓርኩን የተመለከቱ ሰነዶችን በማየት አረጋግጧል። 

በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባህል ድርጅት (ዩኒስኮ) መረጃ መሰረት የዲንደር ብሔራዊ ፓርክ እ.አ.አ በ1935 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን 10,291 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት አለው። ፓርኩ በዩኒስኮ የአለም ቅርስ ጊዜያዊ መዝገብ ቁጥር 6,515 ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ 

የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ ደግሞ በ2006 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን 2,660 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት አለው። “አረንጓዴው ዘብ” በሚል ቅጽል ስም በሚታወቀው በዚህ ፓርክ አናብስትን ጨምሮ ሌሎች የዱር እንስሳሳት ይኖሩበታል። ወቅት እየጠበቁ በፓርኩ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ከብቶችን የሚያሰማሩት ፈላታ በመባል የሚታወቁ ድንበር ተሻጋሪ አርብቶ አደሮች ለፓርኩ ስጋት ስለመሆናቸው በሚዲያዎች በተደጋጋሚ ተዘግቧል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::