“የኒዉክሌር ሃይልን በተመለከተ በሁለቱ ሀገራት መሀከል ያለዉ ስምምነት ኒዉክሌርን ለሰላማዊ ጥቅም ከማዋል ጋር የተገናኘ እንጂ የኒዉክሌር ጦር መሳሪያን የሚያካትት አይደለም”— በኢትዮጵያ የሩስያ ኤምባሲ ለኢትዮጵያ ቼክ ንምክልኻል መን እንታይ ግደ ኣለዎ?

የኢትዮጵያና ሩስያ የኒዉክሌር ዘርፍ ስምምነትን በተመለከተ የተሳሳቱ መረጃዎች እየወጡ ይገኛል። ‘Kanatube/ቃና ቲዩብ’ የተሰኘዉና ከ230 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ገጽ “ሩሲያ በኢትዩጵያ በአፍሪካ ትልቁን የኒኩሌር ማብላያ ልትከፍት ነው” በማለት የካቲት 30/2014 መረጃ አሰራጭቷል።

ይህ በሰበር ዜና መልክ የተሰራጨ መረጃ ‘ዶንግፌንግ 5’ የተሰኘዉን ቻይና ሰራሽ አህጉር አቋራጭ ሚሳኤል የተሸከሙ ተሽከርካሪዎችን ምስልም ተጠቅሟል።

ይህን መረጃ የተመለከቱ በርካታ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ሁለቱ ሀገራት የኑክሌር ጦር መሳሪያ ማምረቻ በኢትዮጵያ ለመገንባት እንደተስማሙ በመዉሰድ የተለያዩ ሃሳቦችን ሲሰጡ ተመልክተናል።

ኢትዮጵያ ቼክ Kanatube/ቃና ቲዩብ ለመረጃዉ ማጠንከሪያነት የተጠቀመዉ ምስል ላይ ባደረገዉ ምርመራ ምስሉ በቻይና ሴንትራል ቴሌቭዥን /CCTV/ ዩትዩብ ቻነል ከሁለት አመት በፊት ከተሰራጨ ቪዲዮ ዉስጥ 38:02ኛ ደቂቃ ላይ (https://youtu.be/ofimgaO7Qck) የተወሰደ የስክሪን ቅጂ (screenshot) መሆኑን አረጋግጧል።

በተጨማሪም በኢትዮጵያና ሩስያ መካከል ስላለዉ የኒዉክሌር ዘረፍ ስምምነት መርጃዎችን የተመለከትን ሲሆን በኢትዮጵያ የሩስያ ኤምባሲንም መረጃ ጠይቀናል።

ኢትዮጵያና ሩስያ እኤአ ሰኔ 2017 አቶሚክ ሀይልን ለሰላማዊ ጥቅም በማዋል ረገድ አብረዉ ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸዉን የሩስያ አቶሚክ ኢነርጂ ኮርፖሬሽን /ROSTAM/ ሰነድ (Russia and Ethiopia) ያመለክታል።

በተጨማሪም ሰነዱ ሀገራቱ የኒውክሌር ሃይል ማመንጫ (Nuclear Power Plant) እና የኒውክሌር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከልን በኢትዮጵያ ለመገንባት ፍኖተ ካርታ እኤአ በ2019 መፈራረማቸዉን ያትታል።

በኢትዮጵያ የሩስያ ኤምባሲ ለኢትዮጵያ ቼክ የላከዉ መረጃም የኒዉክሌር ሃይልን በተመለከተ በሁለቱ ሀገራት መሀከል ያለዉ ስምምነት ኒዉክሌርን ለሰላማዊ ጥቅም ከማዋል ጋር የተገናኘ እንጂ የኒዉክሌር ጦር መሳሪያን የማያካትት መሆኑን ያሳያል።

ስምምነቱ “ኢትዮጵያ የኒዉክሌር ሃይልን እንደ አማራጭ ታዳሽ ሃይል ምንጭ እንድትጠቀም የሚያስችል ነዉ” ይላል የኤምባሲዉ ማብራሪያ።

“በተጨማሪም ኢትዮጵያ በግብርና፤ ጤና እና አምራች ዘርፍ የኒዉክሌር ቴክኖሎጂን እንድትጠቀም የሚያደርግ ነዉ” ብሏል በኢትዮጵያ የሩስያ ኤምባሲ።

ስለዚህም Kanatube/ቃና ቲዩብ ስለ ሀገራቱ ስምምነት አጥጋቢ ማብራሪያ ያለመስጠቱና ለመረጃዉ ማጠንከሪያ የተጠቀመዉ አዉዱን የሳተ ምስል መረጃዉ ሳሳች እንዲሆን አድርጎታል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::