በTIKVAH ETHIOPIA ስም የተከፈቱ የቴሌግራም ቻናሎች!

በቴሌግራም አማካኝነት ወቅታዊ መረጃዎችን ለተከታዮቹ በማድረስ የሚታወቀዉና ከ 1.2 ሚልዮን በላይ ተከታዮች ባሉት TIKVAH ETHIOPIA (https://t.me/tikvahethiopia) ስም የተከፈቱ የቴሌግራም ቻናሎች ማጭበርበር እየፈጸሙ መሆኑን ከተከታታዮቻችን ጥቆማ ደርሶናል።

ይህም “ቲከቫህ ማርኬት” በተሰኘ የቴሌግራም ቻናል “ያልተገደበ የኢንተርኔት ጥቅል አገልግሎት እንሸጣለን” በማለት ሰዎችን በማታለል ገንዘብ እየተቀበሉ እንደሆነ ተከታዮቻችን ነግረዉናል።

አንዱ የኢትዮጵያ ቼክ ተከታይ “ብር በባንክ ተቀብለዉ ይጠፋሉ፤ ከዛን ስልክ አያነሱም” ሲል የደረሰበትን ማጭበርበር ነግሮናል።

ሌላኛዉ ተከታያችን ደግሞ “ብሬን መልስልኝ” ብሎ በመጠየቁ ዛቻ እንደደረሰበት ለኢትዮጵያ ቼክ ነግሯል።

ይህን ጉዳይ በተመለከተ ኢትዮጵያ ቼክ ቲክቫህ ኢትዮጵያን መረጃ የጠየቀ ሲሆን ሲሆን ቲከቫህ ማርኬት የተባለዉ የቴሌግራም ቻናል ከTIKVAH ETHIOPIA ጋር ግንኙነት እንደሌለዉና ተመሳስሎ የተከፈተ አካዉንት መሆኑን ነግረዉናል።

በተጨማሪም ቲክቫህ ኢትዮጵያ ቻናሉ ላይ #TikvahMart እና #TikvahMarket የተባሉ አካዉንቶች ስሙን በመጠቀም በሀሰት እያጭበረበሩ መሆኑን ጽፏል።

በተጨማሪም “አጭበርባሪዎችን ከሚመለከተው አካል ጋር ለይተን ህጋዊ እርምጃ እስከምንወስድ ድረስ ቤተሰቦቻችን እንዲጠነቀቁ በድጋሜ እንገልጻለን” የሚል መረጃ አጋርቷል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::