“ይህ Sudans Post የተባለ ገፅ ብዙ ግዜ የሚያወጣው መረጃ ሀሰተኛ ነው፣ አሁንም ያወጣው ይህ መረጃ ሀሰተኛ ነው”— በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ፒ ሞርጋን

“የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ከአብዬ ግዛት መውጣታቸውን እንደማትቀበል ደቡብ ሱዳን አስታወቀች” የሚል ዜና “Sudans Post” በተባለ ገፅ ከሁለት ቀናት በፊት ወጥቶ ነበር፣ ይህንን ዜናም አንዳንድ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀን ሽፋን ሰጥተውታል።

በዘገባው መሰረት የደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር እና የተመድ የሰላም አስከባሪ ልዑክ አብዬ በሚገኘው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪዎች ሁኔታ ላይ ያተኮረ ውይይት አድርገው ነበር። አክሎም “የደቡብ ሱዳን መንግስት በአወዛጋቢው ክልል ውስጥ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይልን ለመተካት ሱዳን ያቀረበችውን ጥሪ ውድቅ ማድረጎን አስታውቋል” ይላል።

አምባሳደር ጄምስ በዚህ ዙርያ ለኢትዮጵያ ቼክ ዛሬ ያደረሱት መረጃ ግን መረጃው “ሀሰተኛ” እንደሆነ ገልፀው “ይህ ገፅ የሚያወጣው መረጃ ሁልግዜ ሀሰተኛ ነው፣ አሁንም ያወጣው ይህ መረጃ ሀሰተኛ ነው፣ እንደዚህ አይነት ነገር አልተባለም” ብለዋል።

የመረጃው ዋና ምንጭ የሆነው “Sudans Post” ከዚህ በፊትም “ከግብፅ ጋር ባለን ግንኙነት ኢትዮጵያ ጣልቃ አትግባብን ብለው የደቡብ ሱዳን መከላከያ ሚኒስትር ተናገሩ” ብሎ ሀሰተኛ መረጃ አሰራጭቶ ነበር፣ ይህንንም በወቅቱ ለአንባቢዎች አቅርበን ነበር።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::