አንዳንድ የማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች ኤርትራ ሠራዊቷን ከትግራይ ለማስወጣት መስማማቷን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ማስታወቋን የሚገልጽ መረጃ በዛሬው ዕለት ሲያጋሩ ነበር!

ይህም ኤርትራ በኢትዮጵያ ጦርነት መሳተፏን ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ማመኗን እንደሚያሳይም ገልጿል ብለዋል። በተጨማሪም ሌሎች የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ይህን መረጃ አሁናዊ በማስመሰል ሲያጋሩት ተመልክተናል።

ሆኖም ኤርትራ ሠራዊቷን ከትግራይ ለማስወጣት መስማማቷን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አስታወቀች በሚል የተሰራጨው መረጃ አሳሳች መሆኑን ኢትዮጵያ ቼክ አረጋግጧል።

ኤርትራ ሠራዊቷን ከትግራይ ክልል ለማስወጣት መወሰኗን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ያስታወቀችው ልክ የዛሬ አመት እ.አ.አ በ2021 ለምክር ቤቱ በጻፈችው ደብዳቤ ነበር።

እ.አ.አ ሚያዚያ 16 ቀን 2021 ዓ.ም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኤርትራ አምባሳደር ሶፊያ ተስፋማሪያም ለጸጥታው ምክር ቤት የወቅቱ ሊቀመንበር በጻፉት ደብዳቤ በኤርትራ ላይ ተደቅኖ የነበረው ትልቅ ስጋት መቀረፉንና በኢትዮጵያና በኤርትራ ከፍተኛ ባለስልጣናት መካከል በተደረሰ ስምምነት ሀገራቸው ሠራዊቷን ለማስወጣት መወሰኗን ገልጸው ነበር። ደብዳቤው በወቅቱ በኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ድረገጽ ተጋርቶ ነበር።

ይህን ተከትሎ ሮይተርስንና ሌሎች አለም አቀፍ የዜና አውታሮች “ኤርትራ በትግራይ ጦርነት መሳተፏን ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ አመነች” የሚል ርዕስ በመጠቀን በወቅቱ መረጃውን ማሰራጨታቸው ይታወቃል። ስለዚህ ይህንን የሮይተርስ የቆየ ዜና በመጥቀስ ዛሬ የተሰራጨው መረጃ አሳሳች ነበር።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::