በብዙዎች ዘንድ ግራ መጋባትን ያስከተለው የሲዳማ አርነት ንቅናቄ እና የብልግፅና ፓርቲ ቅንጅት!

የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) እና ገዢው የብልግፅና ፓርቲ በመጪው አገራዊ ምርጫ በጋራ ለመወዳደር ያስችለናል ያሉትን ቅንጅት መመስረታቸውን ከሦስት ሳምንት በፊት በሀዋሳ ከተማ በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታውቀው ነበር።

በመግለጫው ሲአንን በመወከል የተገኙት የፓርቲው ዋና ጸሐፊና የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ለገሰ ላንካሞ ሁለቱ ፓርቲዎች ቅንጅት የመሰረቱት በፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 94 መሰረት መሆኑንም ገልጸው ነበር።

ፓርቲዎቹ መቀናጀታቸውን ቢያስታውቁም የቅንጅቱ ስያሜ አለመታወቁ እንዲሁም የሲአን ሊቀመንበር አቶ ዱካሌ ላሚሶን ጨምሮ የፓርቲው አባላት በብልጽግና ፓርቲ ስምና የምርጫ ምልክት በዕጩነት መቅረባቸው በተለይ የሲዳማ ክልል ተወላጆች “ሲአን ከስሟል ወይም ከብልጽግና ጋር ተዋህዷል ወይ?” የሚሉ ጥያቄዎችን በማህበራዊ ትስስር ገጾች ሲያነሱ ኢትዮጵያ ቼክ ተመልክቷል።

ኢትዮጵያ ቼክ ጉዳዩን በተመለከተ ምላሽ ለማግኘት የሲአን የፖለቲካ ጉዳዮች ሃላፊ አቶ ተገኝ ወልዴን አነጋግሯል። ሃላፊው እንደገለጹት “ሲአን አልከሰመም፤ ከብልጽግና ጋር አልተዋሃደም፣ ሲአን በፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 94 መሰረት ከብልጽግና ጋር በሚያግባቡት ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመስራት እንዲሁም በምርጫው አብሮ ለመወዳደር ቅንጅት ፈጥሯል” ብለዋል።

አቶ ተገኝ ለኢትዮጵያ ቼክ እንዳብራሩት ሲአን ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ቅንጅት የፈጠረው የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴን ውሳኔ ተከትሎ ነው። ሁለቱ ፓርቲዎች ቅንጅት የፈጠሩበት ሰነድ ለምርጫ ቦርድ መላኩንና በሁለቱ ፓርቲዎች ፋይል ውስጥ እንደሚገኝም ሃላፊው ገልጸዋል።

አቶ ተገኝ ይህን ይበሉ እንጂ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቅንጅትነት ከመዘገባቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ዝርዝር ውስጥ አልተካተቱም። ኢትዮጵያ ቼክ ከቦርዱ ድረ-ገጽ ባገኘው መረጃ መሰረት በ6ኛው ሀገር ዐቀፍ ምርጫ ላይ ለመወዳደር የምርጫ ምልክቶቻቸውን የመረጡና ከቦርዱ ዕውቅና የተሰጣቸው ፓርቲዎች ዝርዝር ውስጥ በቅንጅትነት የተመዘገበው “ትብብር ለሕብረ ብሔር ዲሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝም (ትብብር)” በሚል ስያሜ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ)፣ የአገው ብሔራዊ ሸንጎ እና የሞቻ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የፈጠሩት ቅንጅት ብቻ ነው።

አቶ ተገኝ የሲአን ዕጩዎች በብልጽግና ፓርቲ ስምና የምርጫ ምልክት ለውድድር ቢቀርቡም ፓርቲዎቹ ህልውናቸውን ይዘው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል። ሃላፊው እንደሚሉት በምርጫው ካሸነፉ ክልሉን በጋራ ለማስተዳደር ከብልጽግና ጋር ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::