ብድር በቀላሉ ማግኘት እንደሚችሉ ከሚገልፁ ሰሞንኛ የማህበራዊ ሚድያ ማስታወቂያዎች ራሳችንን እንጠብቅ!

Scam alert about social media posts advertising fake money lending service ሚድያ

ሐምሌ 24፣ 2015

ብድርን በቀላሉ ካለዋስትና እና ካለብዙ ውጣ ውረድ እንደሚሰጡ የሚገልጹ ማስታወቂያዎች በርከት ባሉ የፌስቡክ ገጾች ሲሰራጩ ተመልክተናል። ማስታወቂያዎቹን የሚያጋሩት ገጾች የተለያዩ ቢሆኑም የሚያሰራጩት ይዘት ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ መሆኑንም አስተውለናል።

ከፌስቡክ ገጾቹ መካከል ‘Goodthingsinformationsharing_au’ ፣ ‘Libby_DE’ ፣ ‘Life Service’ ፣ ‘Familyservice004’ የሚል ስያሜ ያላቸው ይገኙበታል።

ከላይ የተጠቀሱት ገጾች የሚያሰራጯቸውን የብድር ማስታወቂያዎች በክፍያ እንደሚያስተጋቡም (sponsored እንደሚያደርጉ) በግልጽ ይታያል።

በርከት ያሉ የኢትዮጵያ ቼክ ተከታታዮችም የብድር ማስታወቂያዎቹን ታማኝነት እንድናጣራላቸው ጠይቀውናል።

ኢትዮጵያ ቼክ የብድር ማስታወቂያዎችን ትክክለኛነት ለማወቅ በገጾቹ ላይ እና ከማስታወቂያዎች ግርጌ በተያያዙት ድረገጾች ላይ ፍተሻ አድርጓል። እንዲሁም ማስታወቂያ ከፌስቡክ ገጾቹ አስተናባሪዎችን ለማነጋገር ሞክሯል።

በፌስቡክ ገጾቹ ላይ ባደረግነው ክትትል በግልጽ የሚታይ አድራሻ የሌላቸው እና ብድሩን የሚሰጠው አካል ማንነት ያልተገለጸ መሆኑን አስተውለናል። እንዲሁም ገጾቹ ውስን ይዘት  ያላቸው ሲሆኑ በአማርኛ ቋንቋ ከተጋሩት የብድር ማስታወቂያዎች ውጭ ሌሎች ይዘቶች በውጭ ቋንቋዎች የተጻፉ መሆኑን ተመልክተናል።

ከብድር ማስታወቂያዎቹ ግርጌ የተያያዙ ድረገጾችም በግልጽ የተቀመጠ አድራሻ እንደሌላቸው አስተውለናል። ድረገጾቹ  በውጭ ቋንቋዎች የተጻፉ ሲሆን ይዘቶቹም ግልጽነት የጎደላቸውና በማስፈንጠሪያዎች (links) የተሞሉና አጠራጣሪ መሆናቸውን ተመልክተናል።

ኢትዮጵያ ቼክ ከላይ የተጠቀሱትን የፌስቡክ ገጾች አስተናባሪዎችን ለማናገር ሙከራ ያደረገ ሲሆን ምላሽ አላገኘም።

እንደዚህ ባሉ አጠራጣሪ እና ግልጽነት በጎደላችው ገጾች የሚጋሩ “የብድር እንሰጣለን” ማስታወቂያዎችን ከማመናችን በፊት ቆም ብለን እናስተውል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::