“በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ለ20 ሺህ ኢትዮጵያውያን የስራ ዕድል አመቻችቷል” በማለት እየተጋራ ስለሚገኝዉ አሳሳች መረጃ!

‘US Embassy Addis Ababa’ በሚል ስም ከ127 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት የቴሌግራም ቻነል “አሜሪካ ኤምባሲ በጦርነት የተጎዳዉን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለመደገፍና ከክፍለዘመን የዘለቀዉን የአሜሪካና የኢትዮጵያን ወዳጅነት ለማጠናከር ለ20 ሺህ ኢትዮጵያዉያን በአሜሪካ የስራ ዕድል ፈጥሯል” ብሎ መረጃ አጋርቷል።

 

የዕድለኞች የትራንስፖርት፤ የመኖሪያ ቤትና የመኪና ወጪ በኤምባሲዉ እንደሚሸፈንም ጽፏል። 

 

ስለዚህም የዕድሉ ተጠቃሚ መሆን የሚፈልጉ ኢትዮጵያዉያን በቴሌግራም ቻነሉ አማካኝነት እንዲመዘገቡና ተመዝጋቢዎችም ሙሉ ስማቸዉን፤ ስልክ ቁጥራቸዉን እንዲሁም አድራሻና መሰል ግላዊ መረጃዎቻቸዉን እንዲልኩም ይጠይቃል። 

 

የዚህን መረጃ ትክክለኛነትና እዉን የቴሌግራም ቻነሉ የኤምባሲዉ መሆኑን ለማጣራት ኢትዮጵያ ቼክ በኢትዮጵያ የአሜሪካን ኤምባሲን ጠይቋል። 

 

ኤምባሲዉ በአሜሪካ የስራና የቪዛ ዕድሎችን በተመለከተ በተለያዩ ማህበራዊ ትስስር ገጾች ሀሰተኛ መረጃዎች እየተጋሩ መሆኑን አስታዉቋል። 

 

“የአሜሪካ መንግስት በኢሜይል፤ ፌስቡክ ሚሴንጀር፤ ቴሌግራም ወይም ሌላ ማህበራዊ ትስስር ገጾች አማካኝነት ግላዊ መረጃዎችን አይጠይቅም” ብሏል። 

 

ትክክለኛ የስራ ዕድሎችን በድረ-ገጹ ላይ እንደሚለጥፍና ሰዎች ለአጭበርባሪዎች እንዳይጋለጡ ጥንቃቄ እንዲያደርጉም ኤምባሲዉ ጠይቋል። 

 

ይሁን እንጂ ኤምባሲዉ ‘US Embassy Addis Ababa’ የሚል ስምና ከ127 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት የቴሌግራም ቻነል (https://t.me/+FqnK-k2b8-4xZGJk) የእርሱ ስለመሆኑም ሆነ ስላለመሆኑ ያለዉ ነገር የለም።

 

የስራ ዕድል እናመቻቻለን እና መሰል ዘዴዎችን በመጠቀም በተለያዩ ማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚደረጉ የማጭበርበር ድርጊቶችን በብዛት እያየን ነዉ።

 

ስለሆነም የማህበራዊ ትስስር ገጾችንና የመረጃዉን ትክክለኛነት ከመረጋገጣችን በፊት ግላዊ መረጃዎቻችንን ከማጋራትም ሆነ ክፍያዎችን ከመፈጸም እንቆጠብ እንላለን። 

 

መሰል መረጃዎችን ለማየትና ስለተለያዩ መረጃ ማጣሪያ ዘዴዎች ለማወቅ የኢትዮጵያ ቼክን ድረ-ገጽ https://ethiopiacheck.org/ ይጎብኙ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::