“ዜናው የሀሰት ነው”— በኢትዮጵያ የሩስያ ኤምባሲ ለኢትዮጵያ ቼክ 

“Iconic Africa” የተባለ ከ83,000 በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገፅ በትናንትናው እለት ኢትዮጵያ እና ሩስያን በተመለከተ ያወጣው መረጃ የሀሰት እንደሆነ አዲስ አበባ የሚገኘው የሩስያ ኤምባሲ ለኢትዮጵያ ቼክ ያደረሰው መረጃ ያመለክታል። 

ከናይጄርያ የተከፈተው ይህ የፌስቡክ ገፅ በትናንት መረጃው በኢትዮጵያ ያሉት የሩስያ አምባሳደር በኒውክሊየር ሀይል፣ በአካባቢያዊ ፀጥታ እንዲሁም በአውሮፕላን ማምረት ዙርያ ተናገሩት ያለውን መረጃ አጋርቷል። 

“ዜናው የሀሰት ነው። ትክክለኛ መረጃ ሁል ግዜ በኤምባሲው የፌስቡክ ገፅ ላይ እንዲሁም በሌሎች ይፋዊ መንገዶች ይገኛል። በተጨማሪም የአምባሳደሩ ስም በትክክል አልተፃፈም” ያለው ኤምባሲው የሩስያው አምባሳደር የቭገኒ ተርክኺን መሆኑን ገልጿል። 

ኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ ጥቅም ለማዋል በምታደረገው ጥረት ሩስያ ለዘርፉ የሰው ሃይል አቅም ግንባታ ድጋፍ እንደምታደርግ በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ከሳምንት በፊት ተገልጿል። 

ኢትዮጵያና ሩስያ ከዚህ ቀደም የነበሩ ስምምነቶች ወደ ስራ በሚገቡበትና አዳዲስ የስምምነት ማዕቀፎችን መመስረት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያም ምክክር ማድረጋቸው በዚሁ ወቅት ተገልጿል።

ትክክለኛው የሩስያ ኤምባሲ የፌስቡክ ገፅ: https://www.facebook.com/RussianEmbassyinEthiopia/

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::