የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝደንት ፅ/ቤት የትዊተር ገፁ ላይ አስፍሮት የነበረው፣ ሗላ ላይ የቀየረው የህዳሴ ግድብን የተመለከተ ፅሁፍ!

የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝደንት ፌሊክስ ሼስኬዲ በትናንትው ዕለት የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር በተመለከተ ከግብጹ አቻቸው አብዱል ፈታህ አልሲሲ ጋር በስልክ ከተወያዩ በኃላ የፕሬዝደንት ጽህፈት ቤቱ ኦፊሴላዊ የትዊተር አካውንት አወዛጋቢ ትዊት ለጥፎ ነበር።

ትዊቱ “ለማስታወስ ያህል ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የገነባችው ህዳሴ በመባል የሚታወቅ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ በግብጽ እና በሱዳን የመስኖ ስራንና [የውሀ ላይ] ቀዘፋን አስቸጋሪ ያደርጋል” የሚል መልዕክት ይዟል።

የፕሬዝደንት ጽህፈት ቤቱ ይህን ትዊት ዛሬ ያጠፋ ሲሆን ሊቀመንበሩ ለአፍሪቃ አንድነት እና ሰላም የሚበጅ  በመግባባት ላይ የተመሰረተ ስምምነት እንዲደረስ በሙሉ ሃይላቸው እንደሚሰሩ የሚገልጽ አዲስ ትዊት ለጥፏል።

ከሳምንታት በፊት የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበርነትን የተረከቡት ፕሬዝደንት ፌሊክስ ሼስኬዲ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚያደርጉትን የሶስትዮሽ ድርድር ይመራሉ።

ባለፉት ሳምንታት በተለይ ኢትዮጵያና ግብጽ ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር ያላቸውን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ለማጠናከር እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ የተስተዋለ ሲሆን በጥር ወር አጋማሽ ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘዉዴ ወደ ኪንሻሳ በማቅናት ከፕሬዝደንቱ ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።

በዚህ ዉይይት ወቅት ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ከሶስት አስርት ዓመታት በፊት ተዘግቶ የነበረውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኪንሻሳ መልሶ ለመክፈት መወሰኑን “ኪንሻሳ ተመልሰናል” በማለት አስታውቀውም ነበር።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::