በጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግ እና ሮስካ የክፍያ አማራጭ ዙርያ ለቀረቡልን በርካታ ጥያቄዎች ያሰናዳነው ዘገባ! 

ከሰሞኑ በጣም በርከት ያሉ ተከታታዮቻችን ስለ ጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግ ህጋዊነት እንዲሁም ሮስካ የክፍያ አማራጭ በማህበራዊ ሚዲያ  እየተሰራጨ ስለሚገኘው መረጃ እንድናጣራላቸዉ ጠይቀዉናል።  

ኢትዮጵያ ቼክ ጉዳዩን በተመለከተ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ጃርሶ ጎሊሳን እንዲሁም የጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አለማዉ ጋሪን አናግሯል። 

ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸዉን የህብረተሰብ ክፍሎችን የቤት ባለቤት ማድረግን ዓላማዉ ያደረገዉ ጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግ (የማህበር ቤት ልማት) በከተማ አስተዳደሩ እውቅና ያለው ህጋዊ ተቋም መሆኑን የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ጃርሶ ጎሊሳ ለኢትዮጵያ ቼክ ነግረዋል።  

“ከ 2010 ጀምሮ መረጃዎችን በማጣራት፣ ያላቸዉን ፕሮፖዛል በማቅረብ ከኛ ቢሮ ጋር ግንኙነት ነበራቸዉ” ያሉት አቶ ጃርሶ የአከፋፈል ዘዴ እንዴት እንደሚሆን ተጣርቶ፤ የተመዝጋቢዎች ዋስትናም ተረጋግጦ፤ ፕሮጀክቱ በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሳካ ቢቀር እንዴት መደረግ እንዳለበትና ማን ሃላፊነቱን እንደሚወስድ በቢሯቸዉ ህግ አማካሪዎችና ዳይሬክቶሬቶች በኩል ተጣርቶ ወደ ስራ መገባቱን ነግረዉናል። 

ይሁን እንጂ ፕሮፖዛሉ በቢሯቸዉ ተገምግሞ እና ታዉቆ በከተማ ደረጃ ድጋፍ እያደረጉ ያሉት ቤት ፈላጊዎች በቅድሚያ 350 ሺህ ብር፤ መሬቱ በማህበሩ ስም ሲዞር ድግሞ 650 ሺህ ብር ከፍለዉ ቀሪዉን የረጅም ጊዜ የባንክ ብድር ተመቻችቶላቸዉ የቤት ባለቤት የሚሆኑበት የክፍያ አማራጭ እንደሆነ አቶ ጃርሶ ጎሊሳ ለኢትዮጵያ ቼክ ነግረዋል።  

‘ሮስካ’ ስለተባለዉ የክፍያ አማራጭ የጠየቅናቸዉ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ጃርሶ ጎሊሳ ‘ሮስካ’ በጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግ በኩል እየቀረበ ያለ አዲስ ፕሮጀክት እንደሆነ ነግረዉናል። 

ሮስካ ቤት ፈላጊዎች በቅድሚያ ሀምሳ አምስት ሺህ ብር በመክፈል አባል የሚሆኑበትና በየወሩ ደግሞ ሁለት ሺህ ብር ዝግ የባንክ አካውንት ቆጥበዉ የዕጣ ባለዕድል ሲሆኑ የቤት ባለቤት የሚሆኑበት አማራጭ ነዉ፡፡ 

ይሁን እንጂ አቶ ጃርሶ ጎሊሳ ይህ የክፍያ አማራጭ በአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ  እየተገመገመ ያለ እንደሆነ ያስረዳሉ። 

“እየገመገምን እያየነዉ ያለ ነው። በቢሮ ደረጃ በሚገባ ገምግመነዉ፤ በሚገባ ፕሮፖዛሉን አይተነዉ እንደ 350 ሺዉ በሚገባ ካየነዉ በሗላ አዋጭነቱን ለህዝቡ ይጠቅማል በሚለዉ አቅጣጫ ከተግባባን ምናልባት ‘ኢንዶርስ’ እናደርገዉ ይሆናል” ብለዋል። 

በተጨማሪም “ፕሮፖዛሉ ቀርቦልን በልማት ዘርፍ በኩል አይተነዋል። ግን በቢሮ ደረጃም ሆነ በከተማ መስተዳድር ፀድቆ በኛ በኩል አልመጣም” በማለትም አክለዋል። 

በሌላ በኩል የጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አለማዉ ጋሪ ‘ሮስካ’ የግንባታ ክፍያ መክፈል የማይችሉ ሰዎች በቁጠባ የቤት ባለቤት እንዲሆኑ የሚያስችል የክፍያ አማራጭ መሆኑን ይናገራሉ። 

በዚህ የክፍያ አማራጭ ዉስጥ የተካተቱ ቤት ፈላጊዎች በአስር አመታት ዉስጥ በእጣ የቤት ባለቤት እንደሚሆኑ ለኢትዮጵያ ቼክ ነግረዋል።  

“እቁቡ በአስር አመት ነዉ የሚያልቀዉ። እቁቡ ተሰብስቦ ባለአክሲዮኖቹ በየተራ ቤት ይሰራሉ ማለት ነዉ። በአስር አመት ዉስጥ የተመዘገቡት ሰዎች በሙሉ የቤት ባለቤት ይሆናሉ” ብለዋል። 

በሌላ በኩል “ይህ የክፍያ እማራጭ በአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ያልፀደቀ መሆኑ ችግር አያመጣም ወይ?” ብለን ለጠየቅናቸዉ የጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አለማዉ ጋሪ “አያመጣም። እኛ በፍቃዳችን ነዉ እንጂ ከነርሱ ጋር የምንሰራዉ የንግድ ድርጅት ነው። የንግድ ፍቃድ ያለዉ ነዉ። በከተማ መስተዳድር ደረጃም የተደነቀ (appreciate የተደረገ) ነዉ” ብለዋል። 

ለሮስካ የክፍያ አማራጭ ሰዎች መመዝገብና ክፍያ መፈፀም መጀመራቸዉን በተመለከተም “ሰዉ ቢመዘገብም ምንም ክፋት የለውም። ብሎክድ እካዉንት ነዉ። በማንኛዉም ጊዜ ማዉጣት ይችላል” ሲሉ መልሰዋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::