ከዐውድ ውጪ የቀረበ አሳሳች ቪድዮ!

አንዳንድ የማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች ባለፉት ጥቂት ቀናት ጠ/ሚር አብይ አህመድ ከአንድ አመት በፊት የተናገሩትን አንድ ቪድዮ ከዐውድ ውጪ በማቅረብ ሲያሰራጩ ተመልክተናል።

እዚህ ቪድዮ ላይ ጠ/ሚሩ “… እያንዳንዳችን እንሄድበት፣ እንሮጥበት ዘንድ እግር ተሰጥቶ ሲያበቃ እግራችንን መጠቀም ትተን መኪና መጠቀም ከፈጣሪ ጋር የሚያጣላ ነገር ነው። ውሀም ራሱ ህዳሴን መገደብ ጨምሮ ስህተት ነው የሚሆነው፣ ምክንያቱም ውሀውን ከተፈጥሮ ኮርሱ እያወጡ ለኢነርጂ ማዋል፣ ለእርሻ ማዋል ከተፈጥሮ ጋር መጋጨት ነው። ለመሬት ማዳበርያ መጠቀም ከተፈጥሮ ጋር መጋጨት ነው… ቤት መስራትም ጭምር [ከተፈጥሮ ጋር] ሊያጋጨን ይችላል። ከሁሉ በላይ ግን ለምን ጥላ ትይዛላችሁ?” ሲሉ ይደመጣል።

የኢትዮጵያ ቼክ ተከታታዮች ይህ ቪድዮ ትክክለኛ መሆኑን፣ በመቀጣጠል የተሰራ እንደሆነ ወይም በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የተቀናበረ (ዲፕ ፌክ) መሆኑን ወይም አለመሆኑን እንድናጣራ ጥያቄ አቅርበውልናል።

ኢትዮጵያ ቼክ በዚህ ዙርያ ባደረገው ማጣራት ትክክለኛውን (original) ቪድዮ የጠ/ሚር ቢሮ የዩትዩብ ቻናል ላይ ማግኘት ችሏል (ሊንክ)።እዚህ ቪድዮ ላይ ጠ/ሚር አብይ የደመና ማዝነብ ቴክኖሎጂን በተመለከተ የነበረ የሙከራ ትግበራ ፕሮግራም ላይ ንግግር ሲያደርጉ ይደመጣሉ።

በዚህ ንግግራቸው “አንዳንድ ሰዎች ዳመናን ማዝነብ ከፈጣሪ ጋር እንደመጋጨት፣ እንዳልተገባ ልምምድ አድርገው የሚያስቡም አሉ (የቪድዮው 02:35 ጀምሮ)። ይህ በኢትዮጵያ ውስጥ በጣም የተለመደ ነገር ነው” ካሉ በኋላ ከላይ በአሳሳቹ ቪድዮ ተቆርጦ የወጣውን ስለ መኪና፣ ውሀ፣ ማዳበርያ እና ቤት ንግግር ያደርጋሉ።

በመደምደሚያቸው ግን “ተፈጥሮን ለሰው ልጅ ምቹ እንዲሆን አድርጎ መጠቀም ከፈጣሪ ጋር የሚያጣላ አይደለም። ፈጣሪ የእያንዳንዱን ሰው አእምሮ እንዲበለፅግ እና ተፈጥሮን እንዲጠቀም ስለፈጠረ ነው በዘመናት መካከል የሰው ልጅ የአኗኗር ዘይቤ እየተሻሻለ የመጣው። ስለዚህ ደመና ማዝነብም የሚያጋጨን ሳይሆን የተሰጠንን የተፈጥሮ ሀብት መጠቀም ነው” ይላሉ።

ስለዚህ ጠ/ሚሩ ምሳሌ በማድረግ ያቀረቡትን ንግግር ብቻ ነጥሎ ወይም ቆርጦ በማውጣት ማህበራዊ ሚድያ ላይ የተሰራጨው ቪድዮ ከዐውድ ውጪ የቀረበ መሆኑን ማረጋገጥ ችለናል።

ተቀናብረው፣ ከዐውድ ውጪ ተወስደው እንዲሁም ተዛብተው የሚቀርቡ መረጃዎችን፣ ምስሎችን ወይም ቪድዮዎችን ባለማጋራት እና ባለመቀበል የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ተባብረን እንከላከል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::