ዋን ኮንሰልታንሲ: የጉዞ አማካሪ ድርጅት ወይስ ቪዛ የሚያሰጥ ተቋም?

ከሰሞኑ ከተከታታዮቻችን ከደረሱን ተደጋጋሚ ጥያቄዎች መሀል ዋን ኮንሰልታንሲ (One Consultancy) የተባለው ድርጅትን የተመለከተ ነበር። አንዳንዶች “ቪዛ ያሰጣል ተብሎ እየተመዘገብን ነው” ያሉን ሲሆን ሌሎች ደግሞ “የቪዛ ማማከር አገልግሎት ፈልገን ሄድን” ብለው መረጃ ሰጥተውናል። 

ኢትዮጵያ ቼክ ይህንን መረጃ በመያዝ ቀናትን የፈጀ የማጣራት ስራ አከናውኗል። 

በመጀመርያ ከሁለት ግለሰቦች የደረሰን ጥቆማ እንዲሁም ከተመለከትነው አንድ የኮንትራት ውል ቅጂ እንደተረዳነው ዋን ኮንሰልታንሲ “ስራ እና ስራ ነክ ጉዳዮችን ለማስፈፀም” በሚል እስከ 300,000 ብር (ሶስት መቶ ሺህ ብር) ውል እየፈፀመ ይገኛል። በዚህም መሰረት ድርጅቱ ውል በሚፈፀምበት ግዜ 20,000 ብር (ሀያ ሺህ ብር) ቅድመ-ክፍያ ይቀበላል፣ ከዛም “ጉዳዩ” ተብሎ የተገለፀው ስራ በአራት ወር ውስጥ ካልተሳካ በሳምንት ውስጥ ተመላሽ ይሆናል ይላል፣ በተጨማሪም ገንዘቡ ተመላሽ ላይሆን የሚችልባቸውን በዛ ያሉ ነጥቦችንም ያነሳል። 

ታድያ “ስራ እና ስራ ነክ ጉዳዮች” የተባለው ምንድን ነው? 

ዋን ኮንሰልታንሲ በፌስቡክ ገፁ ላይ “ዋን የጉዞ አማካሪ ንግድ ፈቃድ እና እውቅና ያለው ሲሆን 9122 ላይ በመደወል ለትምህርት ወደ ካናዳ፣ ፖላንድ እና ሌሎች የአለማችን ሀገሮች ላይ እንዴት መሄድ እንደሚችሉ  ያማክራል” ይላል። 

ኢትዮጵያ ቼክ ያናገራቸው ሁለት ግለሰቦች ግን “የቪዛ ፕሮሰስ ያስጨርሳል ተብለናል፣ እኛ ዶክመንት ሰጥተናቸው እናስጨርሳለን ብለውን ነው፣ ሲያልቅ ደግሞ ኤምባሲ ገብታችሁ ቪዛችሁን እንድትወስዱ እናስደርጋለን ተብለን ተነግሮን ነው” ይላሉ።  

ኢትዮጵያ ቼክ ያናገራቸው የዋን ኮንሰልታንሲ ስራ አስኪያጅ አቶ መስፍን ገ/ማርያም ደግሞ ይህን ይላሉ: “የኛ ስራ ማማከር ነው። እኛ በትኛውም አይነት መልኩ ቪዛ አናሰጥም፣ ቪዛም አንሰጥም። ከየትኛውም ሀገር ኤምባሲ ጋር የስራ ግንኙነት የለንም፤ ወደ ኤምባሲም አንሄድም። ወደ ኤምባሲ የሚሄደው ባለጉዳዩ ነው። ስራችን የትምህርትና የስራ ዕድል የሚገኝበትን መንገድ ማመላከትና መርዳት ነው። የስራና ሰራተኛ የማገናኘት የኤጀንሲ ስራ አንሰራም። ላማከርንበትና ውል ይዘን ወረቀት ፕሮሰስ ላደረግንበት ሰርቪስ ቻርጅ እናስከፍላለን።” 

አቶ መስፍን ድርጅታቸው ህጋዊ መሆኑን የሚያሳይ የንግድ ፈቃድ ከንግድ ቢሮ እንዳላቸው፣ 9122 ቁጥርን ከቴሌ ያገኙት ከውጭ ጉዳይና ከኢሚግሬሽን ፈቃድ ስላገኙ መሆኑን ነግረውናል። ፈቃዱን ለማየት በኢትዮጵያ ቼክ ሲጠየቁ ግን “በቃል የተደረገ ድጋፍ ነው” የሚል መልስ ሰጥተዋል። 

የድርጅቱ ቢሮ በመገኘት መረጃ የሰበሰበው የኢትዮጵያ ቼክ ባልደረባ ምክር ሲሰጣቸው የነበሩ ሰዎችን ጉዳይ የተከታተለ ሲሆን “ድርጅቱ ቪዛ ያሰጣል” ሲባል ሰምቷል። ቪዛ ለማግኘት የሚያመለክቱ ሰዎች ለአፕል ለቀማ ወደውጭ ሀገራት እንደሚጓዙም ሰምቷል።  

የገንዘቡ ክፍያ የሚያስፈልገው ለአገልግሎት ክፍያ (service charge) መሆኑን እና ይህም ለኤምባሲዎች እና ለዲኤችኤል የሚከፈለውን ይጨምራል እንደተባሉ ያናገርናቸው ሰዎች አስረድተዋል። ካናዳ ከሆነ 300,000 ብር እንዲሁም ፖላንድ፣ ፖርቹጋል፣ ማልታ፣ ቼክ ሪፐብሊክ ወዘተ ከሆነ እስከ 200,000 ብር (ሁለት መቶ ሺህ ብር) ድርጅቱ እንደሚያስከፍል ለመረዳት ችለናል። 

ኢትዮጵያ ቼክ በዚህ ዙርያ የካናዳ ኤምባሲን አነጋግሯል። ኤምባሲው በበኩሉ “ህጋዊ በሆነ መልኩ ስራዎቻቸውን ማስተዋወቅ የሚችሉት የተፈቀደላቸው ወኪሎች ብቻ ናቸው” ይላል። 

“ክፍያ ከሚቀበሉ፣ ነገር ግን ካልተፈቀደላቸው ወኪሎች ጋር አንሰራም” ይላል ስለ ወኪሎች የሚያብራራው የኤምባሲው የድረ-ገጽ ክፍል። ወኪሎች የተፈቀደላቸው ናቸው የሚባሉት በካናዳ ባሉ ሶስት የህግ ማህበራት ውስጥ መስፈርቶችን አሟልተው አባል የሆኑ እንደሆነ ብቻ እንደሆነም ያብራራል።  

እነዚህን እና ሌሎች በዚህ ጽሁፍ ለመግለጽ ፈቃድ ባላገኘንባቸው መረጃዎች ምክንያት፣ ዋን ኮንሰልታንሲ የተባለው ድርጅት ለምሳሌ ከካናዳ ጉዞ ጋር በተያያዘ እነዚህን መስፈርቶች የማያሟላ ድርጅት መሆኑን ማወቅ ችለናል። 

የካናዳ ጉዞዎችን በተመለከተ የበለጠ ለመረዳት ከዚህ በታች ያለውን ሊንክ ይከተሉ እና ራስዎን ከአላስፈላጊ ወጪ ይጠብቁ። 

https://www.canada.ca/en/immigration-refugees-citizenship/services/immigration-citizenship-representative/learn-about-representatives.html

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::