“ኳረንቲን ያደረግነው ነገር የለም፣ በደሴ እንደዚህ አይነት ነገር ተፈጥሮ ከሆነ እናጣራለን”— የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ለኢትዮጵያ ቼክ 

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን (አብን) በመወከል በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ አንድ የምርጫ ክልል የተወዳደሩት አቶ ዘሪሁን ገሠሠ “ሠበር ዜና” በሚል ርዕስ “በደሴ ከተማ 5 ትርፍ የድምጽ መስጫ ሳጥን በድምፅ መስጫ ወረቀት ተሞልቶ መያዙንና ኳራንታይን መግባቱን ምርጫ ቦርድ አስታወቀ፣ ምናልባትም የደሴ ከተማ ምርጫ ሙሉ በሙሉ መሠረዙ የማይቀር ነው” የሚል ጽሁፍ በፌስቡክ ገጻቸው ዛሬ ቀትር ላይ አስነብበው ነበር። 

ይህ ጽሁፍ ከ2.1 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች ባሉት ‘Ethiopian DJ የኢትዮጵያ ሙዚቃ’ የተባለ የፌስቡክ ገጽን ጨምሮ በሌሎች የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች ሲሰራጭ ተመልክተናል። 

ሆኖም ከቆይታ በኃላ አቶ ዘሪሁን ማስተካካያ ያሉትን መልዕክት በፌስቡክ ገጻቸው ለጥፈዋል። አቶ ዘሪሁን ደረሰኝ ባሉት የማስተካከያ መረጃ መሠረት “ቦርዱ በ4 የምርጫ ሳጥኖች ላይ ከተመዘገበው ቁጥር በላይ የመራጭ ካርድ መገኘቱ እንጂ የተገለፀው ሳጥኖቹ ትርፍ ሆነው አደለም” ብለዋል። ጉዳዩን በተመለከተ ውሳኔ ለማሳለፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ከሰዐት ቀጠሮ መያዙንም ጨምረው ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያ ቼክ ጉዳዩን በተመለከ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማብራሪያ የጠየቀ ሲሆን የቦርዱ የኮሚኒኬሽን ሃላፊ ሶሊያና ሽመልስ “ኳረንቲን ያደረግነው ነገር የለም፣ በደሴ እንደዚህ አይነት ነገር ተፈጥሮ ከሆነ እናጣራለን” የሚል ምላሽ አግኝቷል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::