ለአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ከ800 ሺህ በላይ ‘ዲያስፖራዎች’ ድምፅ ሰጥተዋል የሚለው መረጃ ተጋኖ የቀረበ ነው! 

የኢትዮጵያ ፕረስ ድርጅት “ጫናውን ለማስቆም ለባይደን አስተዳደር ድምጽ የሰጡ ከ800 ሺህ በላይ ዲያስፖራዎች መንቀሳቀስ አለባቸው” የሚል ዜና የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበራት ጥምር ሰብሳቢ የሆኑትን ወይዘሮ ሶስና ወጋየሁን ጠቅሶ ዛሬ ፅፏል። 

ሰብሳቢዋ አክለውም “በአሜሪካ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ብቻ ለባይደን መንግስት መመረጥ ከፍተኛ ሆነ ሚና ነበራቸው። ከ800 ሺህ በላይ ኢትጵያውያን የባይደንን አስተዳደር መርጠዋል፤ የኢትዮጵያን ዲያስፖራ ድምጽ ባያገኙ ወደ ስልጣን ላይመጡ ይችሉ ነበር” ብለዋል። 

የዲያስፖራ ኤጀንሲ በበኩሉ ዛሬ ይህንን መረጃ ሲያጋራ “የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ እየፈጠረ ያለውን ጫና ለማስቆም ለባይደን አስተዳደር ድምጽ የሰጡ በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ ዳያስፖራዎች መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ተገለጸ” ብሏል።  

ኢትዮጵያ ቼክ በዚህ ዙርያ መጠነኛ ምርምር ያካሄደ ሲሆን መረጃው ተጋኖ የቀረበ እንደሆነ አረጋግጧል። 

Migration Policy Institute (MPI) የተባለው ተቋም በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን (ልጆቻቸውን ጨምሮ) እ.አ.አ በ 2014 ቁጥራቸው 251,000 ገደማ እንደነበር ፅፏል። 

የአለም አቀፉ የፍልሰተኞች ተቋም (IOM) ደግሞ ሶስት ሚልዮን ገደማ ኢትዮጵያውያን እና ትወልደ ኢትዮጵያውያን እ.አ.አ በ2017 በአለም ዙርያ እንደሚገኙ ይጠቅሳል። ተቋሙ አክሎ 305,000 ገደማዎቹ አሜሪካ ውስጥ እንደሚገኙ ይጠቅስና ይህም ከሰሀራ በታች ካሉ ሀገራት ከናይጄርያ ቀጥሎ ሁለተኛው ነው ይላል። 

የዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ከንቲባ የሆኑት ሙሪየል ቦውሰር የዛሬ ሁለት አመት ገደማ አዲስ አበባን በጎበኙበት ወቅት 350,000 ገደማ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ ይገኛሉ ተብሎ እንደሚገመት ገልፀው የነበረ ሲሆን ከዚህ ውስጥ በዋሽንግተን ዲሲ ብቻ 30,000 የሚጠጉ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አባላት አሉ ብለዋል።  

በመጀመርያ እነዚህ ነጥቦች እንደሚያስረዱት ከ800,000 በላይ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ ይገኛሉ የሚለው መረጃ ተጋኖ የቀረበ ነው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ሁሉም ድምፅ ሰጪዎች ለጆ ባይደን ብቻ ድምፅ ሰጥተዋል ማለት አይቻልም። በመጨረሻም 800,000 ገደማ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ ይገኛሉ ቢባል እንኳን ሁሉም ለፕሬዝደንታዊ ምርጫ ድምፅ መስጠት ይችላሉ ማለት አይደለም፣ ምክንያቱም ድምፅ መስጠት የሚችሉት መስፈርቶችን ማሟላት የሚችሉ ብቻ ናቸው (ዜግነት ያለው፣ እድሜው ለመምረጥ የደረሰ፣ ለመምረጥ የተመዘገበ፣ ወንጀል ሰርቶ በህግ እገዳ ያልተጣለበት ወዘተ)።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::