“… ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገር ትግራይ ጋር በምታደርገው ግጭት…” በሚል ሬውተርስ ያወጣው የተሳሳተ የቪድዮ ዘገባ!

“ድምፃችን ለነፃነታችን እና ለሉዓላዊነታችን” በሚል መሪ ቃል በሺዎች የሚቆጠሩ ታዳሚዎች የተሳተፉበት ሰልፍ በትናንትናው ዕለት በአዲስ አበባ ስታዲዮምና በዙሪያው እንዲሁም በክልል ከተሞች መካሄዱን በርካታ የሃገር ውስጥና የውጭ ሚዲያዎች መዘገባቸው ይታወቃል። ለሰልፉ ሽፋን ከሰጡት የውጭ ሚዲያዎች መሀል የሮይተርስ የዜና ወኪል ይገኝበታል።

ሮይተርስ በዚህ ዙርያ በሰራው የቪድዮ ዘገባ የሰልፉ ዓላማ “… ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገር ትግራይ ጋር በምታደርገው ግጭት…” የአሜሪካ መንግስት ጣልቃ ገብነትን ለማውገዝ መሆኑንን የሚገልጽ አረፍተ ነገር ተጠቅሟል።

ከኢትዮጵያ ህገመንግስት አኳያ ይህ የሮይተርስ ዘገባ የተሳሳተ ነው።

የኢፌድሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 47 ትግራይ በኢትዮጵያ ከሚገኙ 10 ክልሎች (አዲስ ክልል የሆነውን ሲዳማን ጨምሮ) መካከል አንዷ ስለመሆኗ በግልጽ ይደነግጋል። የህገ መንግስቱ አንቀጽ 2 የኢትዮጵያ የግዛት ወሰን የፌዴራሉን አባሎች ወሰን የሚያጠቃልል ሆኖ በዓለም አቀፍ ስምምነቶች የተወሰነ ነው ይላል። በዚህም መሰረት የትግራይ ክልል የኢትዮጵያ የግዛት ወሰን አካል እና አንድ ክልል ነው።

በተጨማሪም የህገ መንግስቱ አንቀጽ 39 ቁጥር 4 የብሔር፣ ብሔረብሔረሰቦች፣ ህዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስከመገንጠል የሚሰጥ ሲሆን ሂደቱንም በግልጽ አስቀምጧል። ይህን አንቀጽ ተግባር ላይ ለማዋል በየትኛውም የኢፌዴሪ አባል ክልሎች እስካሁን ጥያቄ አለመቅረቡ ይታወቃል።

ኢትዮጵያ ከኤርትራ፣ ከጅቡቲ፣ ከሱማሊያ፣ ከኬኒያ፣ ከሱዳን እና ከደቡብ ሱዳን ጋር ትዋሰናለች።

የተሳሳተው የሬውተርስ የቪድዮ ዘገባ (15ኛ ሰከንድ ላይ):
https://twitter.com/Reuters/status/1399070605463408640?s=19

Update

ሬውተርስ ስህተት ያለበትን ቪድዮውን አንስቷል!

ሬውተርስ “… ኢትዮጵያ ከጎረቤት ትግራይ ጋር በምታደርገው ግጭት…” ብሎ ትናንት ያወጣው ቪድዮ ስህተት እንዳለበት ኢትዮጵያ ቼክ ዛሬ መረጃ አቅርቦ ነበር።

የዜና ተቋሙ ይህን የተሳሳተ የቪድዮ ዘገባ ማጥፋቱን ከደቂቃዎች በፊት አስታውቋል። የዜና ተቋሙ ቪድዮው “የጂኦግራፊ ስህተት” እንዳለበት አምኖ ቪድዮውን አንስቷል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::