በዎላይታ ሚድያ ኔትወርክ ተዛብተው የቀረቡ አሳሳች ምስሎች!

ዎላይታ ሚድያ ኔትወርክ (Wolaita Media Network) የተባለና ከ75 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ገጽ በአፍሪካ “ትግራይና ግብጽ” ብቻ ታጥቀውታል ያለውን የአየር መቃወሚያ ሲስተም የሚያሳዩ ሶስት ፎቶዎችን ለጥፏል። በፎቶዎቹ ከአየር መቃወሚያ ሲስተሙ በተጨማሪ ሰንደቅ አላማዎችና ዩኒፎርም የለበሱ ታጣቂዎች ይታያሉ።

እነዚህ ፎቶዎች ከወራት በፊትም በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች ሲሰራጩ የነበሩ ሲሆን ‘Global Defense Corp’ የተባለ ድረገጽ ‘TPLF Captured S-300PMU1 Air Defense System’ በሚል ርዕስ ስር አትሟቸው ነበር።

ኢትዮጵያ ቼክ የፎቶፎረንሲክ መገልገያዎችን በመጠቀም ባደረገው ማጣራት ሶስቱም ፎቶዎች የተነካኩ (photoshoped) መሆናቸውን አረጋግጧል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ቼክ የያንዴክስን የምስሎች መፈለጊያን (Yandex reverse image search) በመጠቀም የፎቶዎቹን ምንጭ ያጣራ ሲሆን ፎቶዎቹ የሩሲያ ጦር ሠራዊት እ.አ.አ ከመስከረም 21- 26/2020 ዓ.ም አስሉክ በተባለ ወታደራዊ ሰፈር ልምምድ ባደረገበት ወቅት ከተቀረጸ ቪዲዮ የተወሰዱ የስክሪን ቅጅዎች (screenshots) መሆናቸውን አረጋግጧል። ስክሪንሾት የተወሰደበት ቪዲዮ: https://www.pizzasmile.ru/watch/yMhgjx43ywE

ማህበራዊ ሚድያ ላይ በቅንብር የሚቀርቡ ምስሎች እየተበራከቱ መጥተዋል፣ እርስዎም ምስሎችን በተለያዩ መተግበርያዎች አማካኝነት ሳያጣሩ ባለማጋራት የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ይከላከሉ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::