አሁንም ራሳችንን ከአታላዮች እንጠብቅ— ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን 

ኮርፖሬሽኑ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ፋኩልቲ እና የንግድ ሥራ ት/ቤት በታህሳስ ወር 2013 ዓ.ም በየሙያ መስኩ እና በየደረጃው ተመዝግበው መስፈርቱን ላሟሉ አመልካቾች ሰጥቶት በነበረው ፈተና ከማለፊያ ውጤት በታች ያገኙ ማለትም ከ 60% በታች ውጤት ያላቸውን ተወዳዳሪዎችን ስልክ እየደወሉ ገንዘብ ክፈሉና እናስቀጥራችኋለን በማለት የሚያታልሉ እና የኮርፖሬሽኑን መልካም ስም የሚያጎድፉ አጭበርባሪዎች እንዳሉ ወደ መ/ቤታችን በመምጣት ካመለከቱ ተወዳዳሪዎች መረዳት መቻሉን በመግለፅ የሚመለከታቸው አካላት ከመሰል አታላዮች እራሳቸውን እንዲጠብቁ ኮርፖሬሽናችን ቀደም ሲል ማሳሰቢያ መስጠቱ ይታወሳል፡፡ 

ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅትም ይህ የማታለል ድርጊት በሌለ መልኩ ቀጥሎ ስልክ እየደወለ ገንዘብ ከከፈላችሁኝ ከኮርፖሬሽኑ አንዱ ፕሮጀክት ወደ ሌላው እንድትዛወሩ አደርጋለሁ የሚል ግለሰብ ስለመኖሩ ይኸው የማታለል ሙከራ ደረሰብን ካሉ ግለሰቦች መረጃ ደርሶናል፡፡ 

በመረጃው መሠረት ይህን የማታለል ሙከራ እያደረገ ያለው ከዚህ ቀደም ኮርፖሬሽኑ በሰጠው ማሳሰቢያ ላይ ረቡኒ ኢሳያስ በሚል ስምና የስልክ ቁጥር 0966459226 በባንክ ሒሳብ ቁጥር 1000338403422 ገንዘብ አስገቡ እና ሥራ አስቀጥራችኋለው እያለ የማታለል ሙከራውን የቀጠለው ይኸው ግለሰብ ገንዘብ ክፈሉና ትዛወሩበታላችሁ በሚል የሚጠቅሰው ፕሮጀክት በአሁኑ ጊዜ ሥራ ላይ የሌለ እና ቀደም ብሎ የተዘጋ ነው፡፡ 

በመሆኑም የሚመለከታችሁ አካላት ይህንኑ በመገንዘብ ከመሰል የመጭበርበር ጥቃት ራሳችሁን እንድትጠብቁ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::