ከትላንት ቀትር ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ “የከተራና የጥምቀት በዓላት ላይ አርማ የሌለው የኢትየጵያ ሰንደቅ አላማ እና ሌሎች ባንዲራዎችን ይዞ መገኘት ክልክል ነዉ” ተብሎ በሚዲያዎች መዘገቡ አንዳንዶችን አነጋግሮ ነበር!

የዚህን መረጃ ምንጭ በተመለከተም የተለያዩ አስተያየቶች በማህበራዊ ትስስር ገጾች ሲንሸራሸሩ ተመልክተናል፣ ተከታታዮቻችንም እንድናጣራ ጥያቄ አቅርበውልናል።

ለምሳሌ ያህል አደባባይ ሚዲያ የተሰኘና ከ20 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት የትዊተር አካዉንት አርማ የሌለዉ አረንጓዴ፤ ቢጫ፤ ቀይ ሰንደቅ አላማን በተመለከተ “ፖሊስ ያልተናገረዉን @ebczena እንደጨመረ እየተነገረ ነዉ” ብሎ ጽፏል።

በርግጥ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (EBC) ግጭት ቀስቃሽ ፅሁፎችን እንዲሁም አርማ የሌለው የኢትየጵያ ሰንደቅ አላማ እና ሌሎች ባንዲራዎችን በበዓላቱ ስፍራ ይዞ መገኘት በፍፁም ክልክል መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስን ጠቅሶ በፌስቡክ ግጹ አማካኝነት ዘግቦ ነበር። ይሁን እንጂ “አርማ የሌለው የኢትየጵያ ሰንደቅ አላማ እና ሌሎች ባንዲራዎችን” የሚመለከተዉን ጽሁፍ ዛሬ ከፌስቡክ ፖስቱ ላይ ማንሳቱን የዜናዉን ማስተካከያ (edit history) በመመልከት ማወቅ ችለናል።

በመቀጠልም የመረጃዉ ባለቤት የሆነዉን የአዲስ አበባ ፖሊስን ፌስቡክ ገጽም ተመልክተናል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ የከተራና የጥምቀት በዓላትን አስመልክቶ በትላንትናዉ ዕለት በፌስቡክ ገጹ ባስተላለፈዉ ምልክት “ከበዓሉ መንፈስና ከህገ-መንግስቱ እንዲሁም ከህግ ጋር የሚቃረኑ የሌላን ወገንን መብት የሚጋፉ መልዕክቶችን እና ግጭት ቀስቃሽ ፅሁፎችን እንዲሁም አርማ የሌለው የኢትየጵያ ሰንደቅ አላማ እና ሌሎች ባንዲራዎችን በበዓላቱ ስፍራ ይዞ መገኘት በፍፁም ክልክል መሆኑን ጥምር የፀጥታ አካላቱ የገለፁ ሲሆን…” በማለት ጽፎ ነበር።

ይሁን እንጂ “አርማ የሌለው የኢትየጵያ ሰንደቅ አላማ እና ሌሎች ባንዲራዎችን” በተመለከተ የተጻፈዉ ጽሁፍ ከተወሰኑ ሰዓታት በሗላ ከፖስቱ ዉስጥ እንዲወጣ ተደርጓል፣ ይህንንም የፖስቱን ማስተካከያ ታሪክ (edit history) በመመልከት ማረጋገጥ ችለናል።

በተጨማሪም “አርማ የሌለው የኢትየጵያ ሰንደቅ አላማ እና ሌሎች ባንዲራዎችን” የሚመለከት ጽሁፍ አስቀድሞ የተጻፈዉ በአዲስ አበባ ፖሊስ ፌስቡክ ገጽ ላይ ሲሆን የተለያዩ ሚዲያና ግለሰቦች ጽሁፉን ማጋራታቸውን ተመልክተናል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::