የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሐይለማርያም ደሳለኝን በተመለከተ ጅግጅጋ ኦንላይን ያወጣው ሀሰተኛ ዘገባ! 

ጅግጅጋ ኦንላይን የተባለው ከ41,000 በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገፅ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሐይለማሪያም ደሳለኝ መጀመርያ ወደ ጣሊያን፣ ሮም ቀጥሎም ወደ አሜሪካ “ሸሹ” ብሎ መረጃ አጋርቷል። 

ገፁ በዘገባው አቶ ሐይለማርያም ወደ አሜሪካ እንዳቀኑ ከወር በላይ እንደሆናቸው ያስነበበ ሲሆን “በህዳሴው ግድብ እና በኢትዮጵያ የፖለቲካ ቀውስ ዙሪያ ከአሜሪካ መንግስት ጋር ጠለቅ ያለ ውይይት አድርገው ነበር…  በዚህም የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መሪዎች ተቀይመዋል” የሚል ፅሁፍ አጋርቷል። 

ኢትዮጵያ ቼክ ይህ መረጃ ፍፁም ውሸት እንደሆነ ዛሬ ማምሻውን ያረጋገጠ ሲሆን አቶ ሐይለማርያም የ2021 African Green Revolution Forum (AGRF) ስብሰባን በናይሮቢ፣ ኬንያ ሆነው እያስተባበሩ እንደሆነ ከራሳቸው ማረጋገጥ ችሏል። 

“እኔ ከትዊተር ውጪ ማህበራዊ ሚድያ ብዙም አልከታተልም” ብለው ለኢትዮጵያ ቼክ የተናገሩት የቀድሞው ጠ/ሚር አቶ ሐይለማርያም “ይህን መረጃ ያወጣውንም ገፅ አላውቀውም፣ እኔ ይህንን የ AGRF ስብሰባ እያዘጋጀሁ ናይሮቢ እገኛለሁ” ብለው መረጃው የሀሰት መሆኑን አጋልጠዋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::