“ለመንግስት ከሚሰጠዉ ክፍያ ዉጭ አንድ ብር ለታርጋ ብሎ መስጠት ሞኝነት ነዉ” ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ለኢትዮጵያ ቼክ

ሰሞኑን ህገ-ወጥ የመኪና ታርጋ አሰጣጥ መበራከቱና ተገልጋዮችም ታርጋ ለማግኘት እስከ 50 ሺህ ብር እየከፈሉ እንደሚገኙ የሚጠቁሙ ጽሁፎች በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ተመልክተናል።

የገጠማቸዉን ችግር ያጋሩንና ጉዳዩን እንድናጣራላቸዉ የጠየቁን ተከታዮቻችንም አሉ።

ኢትዮጵያ ቼክ ጉዳዩን በተመለከተ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ እንዳልካቸዉ ጸጋዬን አናግሯል።

እርሳቸዉም “የታርጋ እጥረት የለም። እንደዉም ከ 18 ሺህ በላይ ትርፍ ታትሞ ክልሎች መጥተዉ እንዲወስዱ በጣም እየጨቀጨቅን ነዉ” ሲሉ የታርጋ እጥረት እንደሌለ ለኢትዮጵያ ቼክ ነግረዋል።

የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣንና ትራንስፖርት ሚኒስቴር ወደ አንድ ተቋም ሲቀላቀሉ ለተወሰነ ጊዜ ክፍተት እንደነበር የሚናገሩት አቶ እንዳልካቸዉ “የስራ ርክክብ ላይ፤ አደረጃጀቱ እስኪስተካከል የተፈጠረ ጋፕ ነበር። አሁን ግን ሁሉም ተቀርፎ ሙሉ ለሙሉ (ችግሩ) ተፈቷል” ይላሉ።

“የመረጃ እጥረትና ቦታዎችን ያለመረዳት ይሆናል እንጂ የታርጋ አሰጣጥ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነዉ” ሲሉም ይናገራሉ።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ህዳር 24/2014 በፌስቡክ ገጹ በለጠፈዉ ማስታወቂያ ለልዩ ልዩ ተስከርካሪዎችና ክልሎች አገልግሎት የሚዉል 18,027 ታርጋዎች በፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት መመረቱን፤ ከዚህም ዉስጥ 4,225 ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አገልግሎት የሚዉል መሆኑን አስነብቧል።

በአዲሱ አሰራር የመኪና ታርጋ የማምረትና ለክልሎች ማከፋፈል ስራ በፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት በኩል የሚሰራ መሆኑን የነገሩን አቶ እንዳልካቸዉ “ምናልባት ክልሎች አዲስ አበባ መጥተዉ ከፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት ወስደዉ ለደንበኞች ከማከፋፈል አንጻር ክፍተት እንዳለ አላዉቅም። ስለዚህ ይሄንን ቼክ ማድረግ ነዉ እንጂ እንደ ፌደራል ግን የተመረተዉ ‘over’ ነዉ” ብለዋል።

በአሁን ሰዓት የታርጋ ፍላጎት ካለ በቀን ከ4,000 በላይ ማምረት እንደሚቻልም የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ ነግረዉናል።

“ታርጋ ለማግኘት ስለሚከፈሉ ያልተገቡ ክፍያዎች”

ለኢትዮጵያ ቼክ ጥቆማ ያደረሱ አንድ ተከታያችን ታርጋ ለመዉሰድ ወደ ክፍለ ከተማቸዉ በሄዱበት ወቅት “አልቋል” እንደተባሉ፤ ይሁን እንጂ ‘በጎን በ50 ሺህ ብር ሲሰጥ’ መመልከታቸዉን ነግረዉናል።

ስለዚህ ጉዳይ የጠየቅናቸዉ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ እንዳልካቸዉ ጸጋዬ “በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ነዉ የምንሰማዉ። እንዲህ ተጠየቅኩ እንዲህ ተደረኩ የሚባል ነገር በአካል የመጣ ነገር የለም” ሲሉ መልሰዋል።

ይህ ጉዳይ ብዥታ እንደፈጠረባቸዉ የሚናገሩት አቶ እንዳልካቸዉ “ከክልሎች ጋር በመደዋወል እየተነጋገርን ነዉ። ‘የተሰጣችሁን ታርጋ አድሉ፤ ተጨማሪ ካለ ጠይቁ፤ ይሄን ነገር አጣሩ’ የሚል መመሪያ ሰጥተናል” ብለዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ቁጥጥር ባለስልጣን በስሩ የሚገኙት ክፍለ ከተሞች የሚያቀርቡትን የታርጋ ፍላጎትን መሰረት በማድረግ ጥያቄ ሲያቀርብ የተጠየቀዉ ታርጋ ታትሞ እንደሚሰጠዉና ባለስልጣኑም ለየክፍለ ከተሞች እንደሚያከፋፍል አቶ እንዳልካቸዉ ያስረዳሉ።

“የፍላጎት ጉዳይ እንጂ የታርጋ እጥረት የለም፤ ያለዉ ማቴሪያልም ተጨማሪ ጥሬ ዕቃ ሳናስገባ ከሁለት አመት በላይ ታርጋ ሊያሳትም የሚችል ሪሶርስ አለ። ከከተማ አስተዳደርና ክልሎች የፍላጎት ጉዳይ፤ የጥያቄ መቅረብ ጉዳይ ነዉ። በቀረበ ልክ ታትሞ ለዛ ክልል ይሰጣል። ይሄ እየተደረገ ነዉ ያለዉ” ብለዋል።

አክለዉም “ለመንግስት ከሚሰጠዉ ክፍያ ዉጭ አንድ ብር ለታርጋ ብሎ መስጠት ሞኝነት ነዉ” ብለዋል።

ተገልጋዮችም እንደዚህ አይነት ብልሹ አሰራር ሲመለከቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በአካል በመገኘት ጥቆማ መስጠት እንደሚችሉ አቶ እንዳልካቸዉ ጸጋዬ ለኢትዮጵያ ቼክ ነግረዋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::