ስናይፐር መሳርያ ይዛ የምትታየው ግለሰብ በአልጀዚራ ዜና ላይ የቀረበችው ሞናሊዛ አብርሀ ነች?

በጃፓን የኤርትራ አምባሳደር የሆኑት እስጢፋኖስ አፈወርቂን ጨምሮ በርከት ያሉ የማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች በቅርቡ አልጀዚራ ላይ የቀረበችው ሞናሊዛ አብረሃ ስናይፐር መሳሪያ ይዛ የሚያሳይ ነው ያሉትን ፎቶ በገጻቸው ላይ ለጥፈዋል።

በማዕከላዊ ትግራይ ዞን የተንቤን አካባቢ ተወላጅ የሆነችው ሞናሊዛ አብርሃ ህዳር 25፣ 2013 አ/ም የኤርትራ ወታደሮች ሊደፍሯት በሞከሩበት ወቅት እጇን በጥይት መመታቷን በመቀሌ ከተማ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ለተገኙ የአልጀዚራ ዘጋቢዎች መናገሯ ይታወቃል። ከደረሰባት ጉዳት በኃላ እጇ እንዲቆረጥ መደረጉን ለአልጀዚራ ቴሌቪዥን ጨምራ ገልጻ ነበር፣ ጉዳቷም በፕሮግራሙ ላይ ታይቷል።

የአልጀዚራ ዘገባን ተከትሎ ሞናሊዛ አብረሃ ስናይፐር መሳሪያ ይዛ የሚያሳይ ነው የተባለ ፎቶ እንዲሁም የትግራይ ክልል ልዩ ሃይል አባል እንደነበረች የሚገልጹ መልዕክቶች በማህበራዊ ሚዲያ በስፋት ተሰራጭተዋል።

ኢትዮጵያ ቼክ በምስሉ ላይ ባደረገው ማጣራት ስናይፐር መሳሪያ ይዛ በፎቶ የምትታየው ወጣት ሴት ሞናሊዛ አብረሃ አለመሆኗን አረጋግጧል።

በርካቶች ሞናሊዛ አብርሀ እንደሆነች ገልፀው ሲለጥፉት የነበረው እና ስናይፐር መሳሪያ ይዛ በፎቶው የምትታየው ወጣት “ለምለም” በሚል ስም የፌስቡክ አካውንት ያላት ግለሰብ መሆኗን ኢትዮጵያ ቼክ ለመረዳት ችሏል።

የዚህ የፌስቡክ አካውንት ባለቤት “ለምለም” ከ5,000 በላይ ተከታይ እንዳላት የተመለከትን ሲሆን “ሞናሊዛ አብርሀ ነች” ተብሎ በቀረበው ምስል ላይ የለበሰችውን ልብስ (ነጭ ቲሸርት እና ቁምጣ) እንዲሁም ስናይፐር መሳርያ እንደያዘች ከሌላ እይታ (angle) የተወሰዱ ምስሎችን ተመልክተናል (ከታች የሚታየው ምስል ላይ 1, 2 እና 3 ይመልከቱ)፣ ነገር ግን በምልከታችን እንዳረጋገጥነው “ለምለም” እና “ሞናሊዛ” ሁለት የተለያዩ ሰዎች ናቸው።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::