“የተፎካካሪ ፓሪቲ አባላት ጊዚያዊ መቀመጫ ፓርላማ ውስጥ እንዲሰጣቸው ገዢው የብልፅግና ፓርቲ ከውሳኔ ላይ ደረሰ” የሚለው ይህ መረጃ እውነታ ይኖረው ይሆን? 

በትናንትናው ዕለት “Daily Mercato”  የተባለና ከ420 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ገጽ  “ሰበር ዜና” በሚል ርዕስ ስር “ተፎካካሪ ፓርቲዎችን አካታች ለማድረግ ፕር ብርሃኑ ነጋን ጨምሮ 60 የተፎካካሪ ፓሪቲ አባላት ጊዚያዊ መቀመጫ ፓርላማ ውስጥ እንዲሰጣቸው ገዢው የብልፅግና ፓርቲ ከውሳኔ ላይ ደረሰ” የሚል ጽሁፍ ለጥፏል። 

ኢትዮጵያ ቼክ ይህ የDaily Mercato ዘገባ የተሳሳተ መሆኑን አረጋግጧል። 

በመጀመርያ የኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 54 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሁሉ አቀፍ፣ ነጻ፣ ቀጥተኛ፣ ትክክለኛ በሆነና ድምጽ በሚስጥር በሚሰጥበት ሥርዐት በየአምስት አመቱ በሕዝብ እንደሚመረጡ ይደነግጋል። ይህ ማለት ብልጽግና ፓርቲ የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት መቀመጫዎችን  የማደለ ስልጣን የለውም። 

ነገር ግን የ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ውጤት  በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ ድምጽ ያገኘው ብልጽግና ፓርቲ በኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 56 መሠረት የመንግስት ሕግ  አስፈጻሚ አባላትን የማደራጀትና የመምራት ስልጣን ያለው ሲሆን በዚህም የተፎካካሪ ፓርቲ አባላትን ማካተት ይችላል። 

ከዚህ ጋር በተያያዘ የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝደንትና የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ፓርቲያቸው አብላጫ ወንበር ማሸነፉን ተከትሎ ባስተላለፉት ረዘም ያለ የጽሑፍ መልዕክት ለሀገርና ለህዝብ ይጠቅማሉ ባሏቸው  የፖለቲካና የኢኮኖሚ አጀንዳዎች ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በመግባባት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::