ይህ የሶማሌ ክልል ቴሌቭዥን (SRTV) ቱርክን በተመለከተ የሰራው ዘገባ ነው?

ሰዳት አይባር የተባለ ከ2,200 በላይ ተከታዮች ያሉት የትዊተር አካውንት የሱማሌ ክልል ቴሌቪዥን (SRTV) ቱርክን የተመለከተ ዘገባ ስለመስራቱ የሚገልጽ መልዕክት ለጥፏል።

ከመልዕክቱ ጋር የሱማሌ ክልል ቴሌቪዥን መለያ (logo) የሚታይባቸው አራት ምስሎችን አያይዟል። ምስሎቹ  ከቴሌቪዥን ስክሪን የተቀዱ (screenshots) የሚመስሉ ሲሆን “ቻይና የኤርዶጋንን ዝምታ እንዴት መግዛት ቻለች” የሚሉ እና ሌሎች ዘገባዎች ጣብያው እንደሰራ የሚገልፁ ምስሎች ቀርበዋል።

ኢትዮጵያ ቼክ የፎቶፎረንሲክ መገልገያን በመጠቀም ባደረገው ማጣራት ምስሎቹ በፎቶሾፕ የተሰሩ መሆናቸውን አረጋግጧል። ኢትዮጵያ ቼክ በተጨማሪ ባደረገው ማጣራት ከሱማሌ ክልል ቴሌቪዥን መለያ ጋር የተቀናበሩት የስክሪን ቅጅዎች “WOIN” ከተባለ የህንድ ቴሌቪዥን ጣቢያ የተወሰዱ መሆናቸውን አረጋግጧል፣ ሊንኩም ይህ ነው https://youtu.be/gJqHD05ZSfY

ሰዳት አይባር የለጠፈውን መልዕክት እና ምስሎች በተመለከተ የሱማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ምክትል ሀላፊ አቶ ፋሩቅ ዋርፋ በትዊተር ገጻቸው ምላሽ የሰጡ ሲሆን ምስሎቹ በፎቶሾፕ የተቀናበሩ እና በክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ ያልተላለፉ መሆናቸውን ገልጸዋል። የሰዳት አይባር ትዊት በሁለቱ አገራት ህዝቦች መካከል መቃቃርን ለመፍጠር ያለመ ነው ሲሉም ጨምረው ጽፈዋል።

አቶ ፋሩቅ የሱማሌ ክልል ቴሌቪዥን የእንግሊዘኛ ቋንቋ መርሐግብር እንደሌለው እና በስክሪን ቅጅው ላይ የምትታየው ዜና አንባቢ የጣቢያው ተቀጣሪ አለመሆኗንም አስፍረዋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::