ይህ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር የተፃፈ ደብዳቤ ነው? 

ዛሬ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ ለደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ እንደተጻፈ የሚገልጽ ደብዳቤ በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲዘዋወር ኢትዮጵያ ቼክ ተመልክቷል። ደብዳቤው “የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ስለመስጠት” የሚል አርዕስት ያለው ሲሆን ደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ የአማራ ተወላጅ ተማሪዎችን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እውቅና ውጭ ምደባ ማካሄዱን እንዲያቆም የሚያስጠነቅቅ የሚል ይዘት አለው። 

ኢትዮጵያ ቼክ የደብዳቤውን ትክክለኛነት ለማጣራት የደብዳቤው ይዘቶች ላይ ምርመራ ያካሄደ ሲሆን ደብዳቤውን ጻፉት የተባሉትን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶንም ማምሻውን አነጋግሯል። 

ደብዳቤው ተጻፈ በተባለበት የታሕሳስ ወር የ2012 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ገና መሰጠት አልተጀመረም ነበር። በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ወደዚህ ዓመት የተሸጋገረው የ2012 ዓ.ም ፈተና ከካቲት 19 ጀምሮ እስከ መጋቢት 2 ቀን 2013 ዓ.ም የተሰጠ ሲሆን ውጤቱ ይፋ የተደረገው በመጋቢት ወር አጋማሽ ነበር። የተማሪዎች የዩኒቨርስቲ ምደባ ደግሞ በሚያዚያ ወር መከወኑ ይታወቃል። ይህ ማለት ደብዳቤው ተጻፈ በተባለበት ታሕሳስ ወር ምንም አይነት የተማሪዎች ምደባ አልነበርም። 

ጉዳዩን በተመለከተ ኢትዮጵያ ቼክ ያነጋገራቸው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ደብዳቤውን እርሳቸው እንዳልጻፉት ገልጸዋል። ዶ/ር ሳሙኤል በታሕሳስ ወር የተማሪዎችን ምደባ የተመለከተ ደብዳቤ ሊጻፍ እንደማይችልም ጠቅሰዋል። 

ደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ ማምሻው በፌስቡክ ገጹ በለጠፈው አጠር ያለ መልዕክትም “ዩኒቨርስቲያችንን በተመለከተ በማህበራዊ ሚዲያዎች የተሰራጩ ወሬዎች አሳሳችና የውሸት መሆናቸውን እንገልጻለን” ብሏል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::