ይህ የትግራይ ኮሚኒቲ ፎረም CNN ላይ አየር ለመግዛት ያስገባው ሰነድ ነው?  

የዛሬ ሶስት ወር ተኩል ገደማ ማህበራዊ ሚድያ ላይ በስፋት ሲዘዋወር የነበረ እና በትግራይ ኮሚኒቲ ፎረም ለCNN የገባ የአየር ሰአት መግዣ ፕሮፖዛል ሰነድ ነው የተባለ ምስል ሰሞኑን በድጋሜ ተከስቷል። በርካቶች ምስሉን እየተቀባበሉት ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ ሰሞኑን በትግራይ ባለው ግጭት ዙርያ ሚድያው የሰራውን ዘገባ አያይዘው “CNN ተከፍሎት ነው” ብለው ፅፈዋል። 

ምስሉ ላይ እንደሚታየው ክፍያው “ለሰብአዊ ቀውስ ግንዛቤ መፍጠርያ” የሚል ሲሆን የትግራይ ኮሚኒቲ ፎረም National Media Spots Inc በተባለ የማስታወቂያ ድርጅት በኩል ለCNN 25,100 ዶላር ገደማ ለአየር ሰአት ለመክፈል ተስማምቶ እንደነበር ይገልፃል። 

ኢትዮጵያ ቼክ የሰነዱን ትክክለኛነት በቀጥታ ከ National Media Spots Inc አረጋግጧል። 

የድርጅቱ ፕሬዝደንት እና ዋና ስራ አስፈፃሚ ሪቻርድ ኤስ ጎልድ ለኢትዮጵያ ቼክ እንዳብራሩት ምስሉ በትክክል ከትግራይ ኮሚኒቲ ፎረም በድርጅታቸው በኩል CNN ላይ የአየር ሰአት ለመግዛት የቀረበ ፕሮፖዛል ነበር። 

አክለውም “በቀረበልን የአየር ሰአት ግዢ ጥያቄ መሰረት ይህን የሚድያ ፕሮፖዛል ሰርተን አቅርበን ነበር፣ ነገር ግን ጠያቂዎቹ መሀል ላይ ትተውት ስለነበር ማስታወቂያው አልተላለፈም፣ ክፍያም አልተፈፀመም፣ በሌላ ማስታወቂያ ድርጅት በኩል ማስታወቂያው ተላልፎ ይሁን አይሁን ግን አላውቅም” የሚል መልስ በኢሜይል ሰጥተዋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::