“የብር ኖት እጥረት ስላለብን ከ10,000 ብር በላይ ለገንዘብ አውጪዎች መስጠት አልቻልንም”— ባንኮች

“የብር ኖት እጥረት ስላለብን ከ10,000 ብር በላይ ለገንዘብ አውጪዎች መስጠት አልቻልንም”— ባንኮች

“የገንዘብ እጥረት የለም፣ እጥረት እንዳለም የደረሰን ሪፖርት የለም”— ብሄራዊ ባንክ ለኢትዮጵያ ቼክ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ከመስከረም 27/2013 አ.ም ጀምሮ ለሁሉም ባንኮች እና አነስተኛ የብድርና ቁጠባ ተቋማት በላከው ደብዳቤ ማንኛውም ግለሰብ በአንድ ቀን ውስጥ ከአንድ ባንክም ሆነ የገንዘብ ተቋም ማውጣት የሚችለው ጥሬ ገንዘብ በ50 ሺህ ብር እንዲሆን አዟል።

በዚሁ አካሄድ ማንኛውም ህጋዊ ሰውነት ያለው፣ ማለትም ተቋማትም ሆኑ የአክስዮን ማህበራት በአንድ ቀን ከአንድ ባንክም ሆነ የገንዘብ ተቋም በጥሬ ማውጣት የሚችሉት ትልቁ ገንዘብ 75 ሺህ ብር መሆኑን እንዲሁ መመሪያው አስቀምጧል።

ይህ አሰራር ከባንኮች ውጪ ያለ ገንዘብን ወደ ተቋማቱ ለማምጣት ያለመ እንደሆነ በወቅቱ በሚድያዎች ተነግሯል።

ይሁንና አሁን ላይ በርካታ ባንኮች ገንዘብ ማውጣት ለሚፈልጉ ተገልጋዮቻቸው እየሰጡ ያሉት ለ10,000 ብር፣ በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ 5,000 ብር እንደሆነ ኢትዮጵያ ቼክ ተመልክቷል። ይህም በተለይ ብዙ ብር ለሚያንቀሳቅሱ እና ክፍያ ለሚፈፅሙ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ከፍተኛ ችግር እየሆነ እንደመጣ ታይቷል።

ምክንያቱ ምን እንደሆነ ኢትዮጵያ ቼክ ያነጋገራቸው ባንኮች “የብር ኖት እጥረት” እንደሆነ በተመሳሳይ መልኩ ተናግረዋል። የአንድ የግል ባንክ ምክትል ስራ አስኪያጅ “በተለይ ከብር ለውጡ ወዲህ እየደረሰን ያለው የብር ኖት መጠን አነስተኛ ነው፣ ስለዚህ አመጣጥነን በመስጠት ሁሉም ለማስተናገድ እየሞከርን ነው። ይልቅ በኤቲኤም እስከ 10,000 ብር በቀን ማውጣት ስለሚቻል ብዙዎች እሱን እየተጠቀሙ ይገኛሉ” ብለዋል።

በጉዳዩ ዙርያ ኢትዮጵያ ቼክ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዢ ዶ/ር ይናገር ደሴ የብር ኖት እጥረት እንደሌለ ያስረዳሉ።

“እጥረት የለም፣ ባንኮች በሚጠይቁን መሰረት የብር ኖቶችን እያከፋፈልን ነው። የብር ኖት እጥረት እንዳለ የሚያመለክት ሪፖርትም እስካሁን አልደረሰኝም” ብለዋል።

በቅርቡ ለተደረገው የብር ቅያሬ 3.7 ቢልዮን ብር እንደወጣ የተገለፀ ሲሆን በቅያሬው ምክንያት ደግሞ 14 ቢልዮን ብር ወደ ባንኮች እንደገባ ብሄራዊ ባንክ አስታውቆ ነበር።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::