“የኤምባሲውን መዘጋት በተመለከተ የተጋራው መረጃ ዉሸት ነዉ”— አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለኢትዮጵያ ቼክ

“ኢትዮጵያ በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘዉ ኤምባሲዋን ዘጋች” የሚል መረጃ በማህበራዊ ትስስር ገፆች በስፋት እየተጋራ ይገኛል። 

መረጃውን “ባቲ ፖስት” የተባለ ከ457,000 በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ገፅ “ዶ/ር ብርሀነመስቀል አበበ ሰኚ” የተባሉ የቀድሞ ዲፕሎማትን ጠቅሶ አጋርቷል። 

ገፁ ባቀረበው ፅሁፍ “ከአምባሳደሩ በስተቀር በኤምባሲው ውስጥ ያሉ ከፍተኛ ዲፕሎማቶችን ጨምሮ በኤምባሲው የሚሰሩ ወደ 18 የሚጠጉ ሙያዊ ዲፕሎማቶች ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው እንዲመጡ ተነግሮቸዋል” ያለ ሲሆን አክሎም “በተጨማሪም አምባሳደሩን ብቻ በመተው በኒውዮርክ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ዋና መሥሪያ ቤት የኢትዮጵያን ቋሚ ተልዕኮ ዘግቷል” ብሏል። በዚህ መረጃ መሰረት በካናዳ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲም አምባሳደሩ ብቻ ወደ ኋላ ቀርተው የተዘጋ መሆኑን አስነብቧል። 

ስለ ጉዳዩ የፃፉ ሌሎች የማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎችም ኢትዮጵያ በአሜሪካ የሚገኘዉን ኤምባሲዋን መዝጋቷን እንዲሁም በኤምባሲዉ የሚሰሩ ዲፕሎማቶቿን መጥራቷን ፅፈዋል። 

ኢትዮጵያ ቼክ በጉዳዩ ዙርያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲን ያናገረ ሲሆን የኤምባሲውን መዘጋት በተመለከተ የተጋራው መረጃ “ዉሸት ነዉ” ብለዋል።  

ዲፕሎማቶች ተጠርተዋል ለሚለዉም “ዲፕሎማት ለስራ ይጠራል፣ ይሄዳል። ይሄ ኖርማል ነው፣ ምንም አዲስ ነገር አይደም” በማለት መልሰዋል። 

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ፍፁም አረጋ በትናንትናው እለት በዳላስ፣ ቴክሳስ በነበረ ፕሮግራም ላይ ተገኝተው እንደነበር መረጃ አጋርተዋል። 

አዲስ ፎርቹን ጋዜጣ ሐምሌ 17/2013 ባስነበበው ፅሁፍ ከአምባሳደሮች እና የፋይናንስ ሀላፊዎች ውጪ ያሉ ዲፕሎማቶች ወደ ሀገር ቤት እንደተጠሩ አስነብቦ ነበር። ጋዜጣው በወቅቱ በፅሁፉ እንዳሰፈረው ዲፕሎማቶቹ የተጠሩት ለስልጠና እና አዲስ የስራ አመራር ለመቀበል ነው።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::