የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ የተናገሩት ምን ነበር?

በትላንትናዉ እለት AradaNet.com የተሰኘ የፌስቡክ ገጽ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ “አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የኦሮምያ ክልልን በአንድ ወር ግዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ወደ ቀድሞ ሰላሟ እንመልሳታለን” ሲሉ ለጨፌ ኦሮሚያ ተናግሯል በማለት መረጃ አጋርቷል።

በርካታ የፌስቡክ ተጠቃሚዎችም AradaNet.com ባሰራጨዉ መረጃ ስር ሃሳባቸዉን (ኮመንት) ሲጽፉ እንዲሁም መረጃዉን ሲያጋሩ ተመልክተናል። የኢትዮጵያ ቼክ ተከታዮችም ጉዳዩን እንድናጣራ ጠይቀዉናል።

ፕሬዝዳንቱ በጉባኤዉ የክልሉን አስፈጻሚ አካል የ2014 ዓ.ም የሰባት ወር አፈጻጸም ሪፖርት ሲያቀርቡም ሆነ ከጨፌዉ አባላት ለቀረቡላቸዉ ጥያቄዎች መልስ ሲሰጡ ይህን ንግግር እንዳልተናገሩ ኢትዮጵያ ቼክ ያረገው የቪድዮ ዳሰሳ አረጋግጧል።

ይሁንና ፕሬዝዳንቱ በወቅቱ “ህዝባችንና አደረጃጀታችን አንድ ሆኖ አቋም ከያዘ ሸኔ አንድ ወር መቆየት አትችልም” ብለው ተናግረዋል፣ ይህ ደግሞ “አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የኦሮምያ ክልልን በአንድ ወር ግዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ወደ ቀድሞ ሰላሟ እንመልሳታለን” ከሚለው የተለየ ነው።

ፕሬዝደንቱ አክለው “የምትታገልበት የፖለቲካ አላማ የላትም። ሰዉን የምታሰልፍበት የፖለቲካ አጀንዳ የላትም፤ ህዝብን እያሳቀቀች ነዉ ለማሰለፍ እየሞከረች ያለችዉ። ስለዚህ በሰራችዉ ስራ ስለተጋለጠች ይህን ሀይል ፊቱ ቆመን፤ በሚፈለገዉ ደረጃ ታግለን መንገድ ለማስያዝ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ከየትኛዉም ጊዜ በላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት ያለ ጉዳይ ነዉ” ብለዋል።

በጉባኤዉ ላይ የክልሉን ሰላምና ድህንነት ችግር በተመለከተ በርካታ ጥያቄዎች የቀረቡላቸዉ ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::