አይኤምኤፍ በዩክሬን እና ሩሲያ ግጭት ምክንያት ኢኮኖሚያቸው ለተጎዳ የአፍሪካ ሀገራት 50 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ሊያደርግ ነው በሚል ኢቢሲ ዛሬ የሰራው ዜና የተሳሳተ ነው! 

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በዘገባው የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ ከአለም አቀፍ ጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ይህን እንደተናገሩ ሚድያው ጠቅሷል። 

ዘገባው አክሎም “ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን አገሮች የመቋቋም አቅምን ከፍ ለማድረግ በዘላቂነት እንዲያገግሙ ለማበረታታት ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም 50 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብቷል” ይላል።  

ኢትዮጵያ ቼክ ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ ከጋዜጠኞች ጋር ያደረጉትን ቆይታ የተከታተለ ሲሆን የኢቢሲ ዘገባ የተሳሳተ እንደሆነ አረጋግጧል። 

ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ ለጋዜጠኞች ያሉት “የአፍሪካ ሀገራት የሪፎርም/ለውጥ ስራዎችን አከናውነው እና የአይኤምኤፍ መስፈርቶችን አሟልተው ከተገኙ ተቋሙ Resilience and Sustainability Trust (RST) በሚል ካዘጋጀው ፕሮግራም 50 ቢልዮን ዶላር ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ” የሚል ነው። 

ይህ RST የተባለው ፕሮግራም የሩስያ እና ዩክሬን ግጭት ከመከሰቱ አራት ወር በፊት ገደማ (ዲሴምበር 2021 ላይ) ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሀገራት የኮሮና ቫይረስ፣ የአየር ጠባይ ለውጥ እና በዲጂታላይዜሽን ወደኋላ መቅረት ካመጣው ጫና ለመላቀቅ የሚያደርጉትን ጥረት ለመደገፍ የተቋቋመ ነው። 

ስለዚህ ይህ የአይኤምኤፍ የ50 ቢልዮን ዶላር ታሳቢ ድጋፍ ከሩስያ እና ዩክሬን ጦርነት ጋር የተያያዘ እንዳልሆነ መገንዘብ ይቻላል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::