“እኔ በስራዬ ላይ እገኛለሁ፣ ጥገኝነት ለመጠየቅ የሚያበቃ ነገር አልነበረም፣ አሁንም የለም”— በጣልያን የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሚቱ ሀምቢሳ 

ከጥቂት ቀናት ወዲህ ማህበራዊ ሚድያ ላይ በጣልያን የሚገኙት የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሚቱ ሀምቢሳ ያሉበት ጣልያን ሀገር ውስጥ ጥገኝነት እንደጠየቁ የሚገልፁ በርካታ ፅሁፎችን ተመልክተናል። 

በተመሳሳይ አንዳንድ የማህበረሰብ ሚዲያ ተጠቃሚዎች “በጣልያን ሮም የኢፌዲሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ደሚቱ ሃምቢሳ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ የተደረገላቸዉን ጥሪ ባለመቀበል በጣልያን ሀገር ጥገኝነት ጠየቁ” በማለት እየፃፉ ይገኛሉ።  

በርካታ የኢትዮጵያ ቼክ ተከታታዮችም ይህን እንድናጣራ ጥያቄ አቅርበዋል። 

ዛሬ አምባሳደር ደሚቱን በስልክ አግኝተናቸው ተከታዩን መረጃ ለኢትዮጵያ ቼክ ሰጥተዋል: 

“እኔ በስራዬ ላይ እገኛለሁ፣ ጥገኝነት ለመጠየቅ የሚያበቃ ነገር አልነበረም፣ አሁንም የለም። እኔም ማህበራዊ ሚድያ ላይ ተፅፎ አይቼዋለሁ፣ ሳየው በጣም ነው የገረመኝ። ፍፁም ውሸት ነው፣ እንደዛ ማሰባቸው ራሱ ያሳዝናል” ብለዋል። 

አክለውም “ዛሬ እንኳን በጣልያን ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት እያረግን ነው፣ ውይይቱ ነገም ይቀጥላል። ምናልባት በጣልያን ያለው የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ እያረገ ያለው በጎ እንቅስቃሴ ያበሳጫቸው ሊሆኑ ይችላሉ” ብለው ማብራርያ ሰጥተዋል። 

ኢትዮጵያ ቼክ በጉዳዩ ላይ የኢፌዲሪ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስርቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲንም በዚህ ዙርያ አናግሯል።  

አምባሳደር ዲና “መንግስት እንደ ሌሎች ተቋማት ኤምባሲዎችን ሪፎርም ለማድረግ የጀመረዉ ስራ አለ።  ይህን ሪፎርም ምክንያት አድርገዉ ነዉ ይህ የሀሰት መረጃ /disinformation/ እየተሰራጨ ያለዉ” ብለዋል። 

በተመሳሳይ ሁኔታ “አምባሳደር ዘነቡ ታደሰ ጥገኝነት ጠይቀዋል” የሚሉ ፅሁፎች እየተጋሩ እንደሆነ የተናገሩት ቃል አቀባዩ ይህ ሀሰት መሆኑንና አምባሳደሯ ስራ ላይ መሆናቸዉን  ለኢትዮጵያ ቼክ ነግረዋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::