የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ እቃዎችን በመተካት ከ114 ቢሊየን ዶላር በላይ ማዳኑ ትክክለኛ ዜና ነው? 

ኮርፖሬሽኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ እቃዎችን በሀገር ውስጥ በመተካት ከ114 ቢሊየን ዶላር በላይ ማዳኑን አንዳንድ ሚድያዎች ዛሬ ዘግበዋል። 

ይህን የተጋነነ ቁጥር ተመርኩዞ ኢትዮጵያ ቼክ የሚድያ ዳሰሳ ያደረገ ሲሆን “114 ቢሊየን ዶላር” ተብሎ የቀረበው “113 ሚልዮን ዶላር” እንደሆነ ለማረጋገጥ ችለናል። 

የቢዝነስ ዘገባዎችን በማቅረብ የሚታወቀው ኢትዮ የንግድ እና ኢንቨስትመንት መድረክ ይህንን የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የ9 ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ተከታትሎ የሰራውን ዘገባ ተመልክተናል። 

ሪፖርቱን ያቀረቡት የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳንዶካን ደበበ እንደተናገሩት ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚገኙ አምራቾች ለሀገር ውስጥ ገበያ ከ113 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚገመቱ ምርቶች አቅርበዋል። 

አክለውም ባለፉት 9 ወራት ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ምርት ኤክስፖርት 152 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን፣ ይህም በብር ሲተመን 7.5 ቢሊዮን ብር ነው ብለዋል። በተጨማሪም 44 ሺህ አዳዲስ የስራ እድሎች ባለፉት 9 ወራት እንደተፈጠሩ ገልጸዋል። 

ይሁን እንጂ በኮቪድ እና በሰሜኑ ጦርነት ተፅእኖ ምክንያት ስራ ያቆሙ 3 ኢንዱስትሪ ፓርኮች ማለትም መቀሌ፣ ጅማ፣ ባህርዳር አና ስራ ያልጀመረው ሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርኮች  ሳቢያ መገኘት ያለበት ገቢ ሊገኝ አለመቻሉን አስታውቀዋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::