“የተናገርኩት ነገር የለም፣ ስለጉዳዩም የማውቀው ነገር የለም”— ፕ/ር መረራ ጉዲና ለኢትዮጵያ ቼክ

በትናንትናው ዕለት በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና “እራሳቸውን ገሰጹ!” የሚል ጽሁፍ ሲዘዋወር ተመልክተናል። 

ጽሁፉ “የብልጽግና መንግሥት በፓርቲያችን እና በአመራሮቻችን ላይ የፈጸመው ድርጊት ባሳደረብን ሕመም ለሕዝባችን የማይመጥኑ ውሳኔዎችን ስናስተላልፍ መቆየታችን ይታወቃል” በማለት ይጀምርና “በእውነቱም በዚህ ሰዓት ስለ ሽግግር  መንግሥት ማሰብ ከአራት ዓመት በፊት የሕይወት መስዋዕትነት በከፈሉ ቄሮዎች መካነ መቃብር ላይ ተረማምዶ ከገዳያቸው ጋር እንደመደራደር የሚቆጠር ነው” የሚል የሚል ዐረፍተ ነግር አካቷል። 

ኢትዮጵያ ቼክ ይህ በስፋት የተጋራ ጽሁፍ በእርሳቸው የተነገረ መሆኑን ለማረጋገጥ ፕሮፌሰር መረራን አነጋግሯል። 

“የተባለውን ጽሁፍ እኔም ፌስቡክ ላይ ነው ያየሁት። የተናገርኩት ነገር የለም፣ ስለጉዳዩም የማውቀው ነገር የለም” ሲሉ ለኢትዮጵያ ቼክ ገልጸዋል። 

በተጨማሪም ፕሮፌሰር መረራ እርሳቸውን ጨምሮ በሌሎች ታዋቂ ግለሰቦች ሊመሰረት ታስቧል እየተባለ ስለሚነገረው የሽግግር መንግስት የሚያውቁት ነገር እንደሌለም ተናግረዋል። የሽግግር መንግስት ሊመሰርቱ ነው ተብለው ስማቸው ከሚጠቀሱ ግለሰቦች ጋር ከተገናኙ ረጀም ጊዜ መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰር መረራ ከአንዳንዶች ጋር በጭራሽ ተገናኝተው እንደማያውቁም አስረድተዋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::