“አሜሪካ የህክምና ክትትል እያደረግኩ፣ እዛ በሚገኘው ቢሯችን እየተገኘሁም ስራዬን እየሰራሁ እገኛለሁ”— አቶ ተወልደ ገ/ማርያም ለኢትዮጵያ ቼክ

ከሰሞኑ በርካታ የማህበራዊ ሚድያ ገፆች፣ አካውንቶች እና ቻናሎች የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ተወልደ ገ/ማርያም ከስራቸው እንደለቀቁ፣ በውጪ ሀገር ጥገኝነት እንደጠየቁ እንዲሁም ከስራ ታግደው አዲስ አበባ ውስጥ እንደሚገኙ የተለያዩ ፅሁፎችን ሲያጋሩ ተመልክተናል።

በዚህ ዙርያ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ኢትዮጵያ ቼክ አቶ ተወልደን እንዲሁም አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የስራ ባልደረባቸውን መረጃ ጠይቋል።

አቶ ተወልደ “አሜሪካ የህክምና ክትትል እያደረግኩ፣ እዛው በሚገኘው ቢሯችን እየተገኘሁም ስራ እየሰራሁ እገኛለሁ” የሚል አጠር ያለ ምላሽ ሰጥተዋል። የስራ ባልደረባቸው የሆኑት ግለሰብም ይህንን አረጋግጠው “ማህበራዊ ሚድያ ላይ የሚፃፈውን እኔም እያየሁ ነበር፣ ፍፁም ውሸት ነው” ብለው መልስ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ ቼክ በተጨማሪ አየር መንገዱ እስከ ቅርብ ቀናት ድረስ ያወጣቸውን ጋዜጣዊ መግለጫዎች የተመለከተ ሲሆን ከትናንት በስቲያ አርብ (ታህሳስ 15/2014) የወጣ መግለጫ ላይ እርሳቸው እንደ ዋና ስራ አስፈፃሚ የተጠቀሱበት እና አስተያየት የሰጡበት መግለጫን ተመልክቷል።

ስለዚህ በዚህ ዙርያ ሲሰራጩ የነበሩ መረጃዎች ከሶስት አቅጣጫ ሲታዩ ሀሰተኛ እንደሆኑ መገንዘብ ይቻላል።

ያልተረጋገጡ፣ ማስረጃ ያልቀረበባቸውን እና ሀሰተኛ መረጃዎችን ባለማጋራት የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ይቀንሱ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::