“እንዴት በአውቶብስ እንሄዳለን? የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኛ መሆኑ መረሳት የለበትም”— የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ለኢትዮጵያ ቼክ

‘Karim Ahmed Farg’ የተባለ ግብጻዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ለ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ ወደ ካሜሮን ያቀናው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ስፍራው በአውቶብስ መጓዙን የሚገልጽ ጽሁፍ በፌስቡክ ገጹ ላይ አስፍሮ ነበር።

ጋዜጠኛው የአውቶብሱ ጉዞ 84 ሰዐት እንደወሰደም የጠቀሰ ሲሆን ከኢትዮጵያውያንና ከሌሎች ተከታዮቹ ትችት ከደረሰበት በኃላ መልዕክቱን አጥፍቷል።

ሆኖም ጋዜጠኛው ያሰፈረው መልዕክት በተለይ የፈረንሳይኛ ተናጋሪ በሆኑ አፍሪካውያን የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች እንደገና መሰራጨቱን ተመልክተናል። መልዕክቱን ካሰራጩት መካከል ከ14 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት ‘Coupe d’Afrique des Nations 2021’ የተባለ የትዊተር አካውንት ይገኝበታል።

ኢትዮጵያ ቼክ ጉዳዩን ለማጣራት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁንን ያናገረ ሲሆን የተሰራጨው መልዕክት ሀሠተኛ መሆኑን ነግረውናል።

አቶ ባህሩ “እንዴት በአውቶብስ እንሄዳለን? የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኛ መሆኑ መረሳት የለበትም” በማለት ስለጉዞው ዝርዝር ሁኔታ በፌድሬሽኑ የፌስቡክ ገጽ መቀመጡን ነግረውናል።

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መረጃ መሰረት ብሔራዊ ቡድኑ ባለፈው እሁድ 3:15 ላይ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፍያ በመነሳት የካሜሮኗ ዱዋላ ከተማ ደርሶ ለአንድ ሰዓት ከቆየ በኋላ 10:30 ገደማ ወደ ዋና ከተማዋ ያውንዴ ደርሷል። የተጓጓዘውም በኢትዮጵያ አየር መንገድ መሆኑ ተገልጿል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::