በኢትዮጵያ ባለፉት 40 ዓመታት ከ74 ሚልዮን በላይ ሰዎች ኤች አይ ቪ/ኤድስ በደማቸዉ ውስጥ ተገኝቷል? 

በትናንትናዉ እለት ‘Fidel Media ፊደል ሚዲያ’ የተሰኘ የዩትዩብ ቻናል “በኢትዮጵያ ባለፉት 40 ዓመታት ከ74 ሚልዮን በላይ ሰዎች በ ኤች አይ ቪ/ኤድስ ተይዘዋል። ከነዚህ ዉስጥም 36 ሚልዮን ወይም ለግማሽ የተቃረበ ቁጥር ያላቸዉ ሰዎች ለሞት መዳረጋቸዉ ታዉቋል” በማለት ዘግቧል። 

ፊደል ሚዲያ ለዚህ መረጃዉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤትን በምንጭነት ተጠቅሟል። 

ኢትዮጵያ ቼክ ይህን መረጃ  በተመለከተ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት ፕሮግራም ዳይሬክተር የሆኑትን ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌን አናግሯል። 

እርሳቸዉም “መረጃዉ ትክክል አይደለም፤ እኛ እንደዛ አይነት መረጃ አልሰጠንም” በማለት ለኢትዮጵያ ቼክ ነግረዋል።  

በሌላ በኩል መረጃዉ በጣም የተጋነነ እንደሆነ ለኢትዮጵያ ቼክ የነገሩት በፌደራል ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል በትረ “ባሁኑ ሰዐት በኢትዮጵያ ከ600 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ኤች አይ ቪ በደማቸዉ ይገኛል” ብለዋል።  

በተጨማሪም እንደ ሀገር አቀፍ በየ አመቱ ከ11,000 በላይ ሰዎች በኤች አይ ቪ እና ተያያዥ በሽታዎች ህይወታቸዉ ሲያልፍ ከ10ሺ በላይ ደግሞ በኤች አይ ቪ  እንደሚያዙ አቶ ዳንኤል ነግረዉናል።  

ኤች አይ ቪ ኤድስ በኢትዮጵያ ከተገኘ ጊዜ ጀምሮ ቫይረሱ በደማቸዉ የተገኘ ሰዎች ቁጥር ስንት እንደሆነ የጠየቅናቸዉ ሲሆን የዚህ ቁጥር ግምት መረጃ ለጊዜዉ እንደሌላቸዉ ተናግረዋል።  

እንደ አለም አቀፍ ጤና ድርጅት መረጃ ኤች አይ ቪ ኤድስ ከተገኘ ጊዜ ጀምሮ 79.3 ሚልዮን ሰዎች ቫይረሱ በደማቸዉ ተገኝቷል፤ 36.3 ሚልዮን ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ሞተዋል። 

በተጨማሪም በፈረንጆቹ 2020 በአለም አቀፍ ደረጃ ኤች አይ ቪ ኤድስ በደማቸዉ የሚገኘ ሰዎች ቁጥር 37 ሚልዮን እንደሆነ የአለም አቀፍ ጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::