በኢትዮጵያ ፕረስ ድርጅት እና ዋልታ “ጆርጅ ቦልተን” ተብሎ የቀረበው ምስል ጉዳይ!

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዛሬ በአማርኛ፣ በትግርኛ እና በእንግሊዝኛ የፌስቡክ ገጾቹ ጆርጅ ቦልተን የተባሉ “የቀድሞ የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ ኃላፊ” በትዊተር ገጻቸው አስተላለፉ ያለውን መልዕክት የስክሪን ቅጅውን በማያያዝ ለጥፏል። ትንሽ ቆይቶ ዋልታም በማህበራዊ ሚድያው ላይ ተመሳሳይ መረጃ አጋርቷል።

በዜናዎቹም “የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ሽግግር ያደናቅፋል” ብለው እኚህ ግለሰብ እንደተናገሩ እነዚህ ሁለት ሚድያዎች ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እና ዋልታ ጆርጅ ቦልተን የፖለቲካ ተንታኝ እንደሆኑ እንዲሁም በሰብአዊ ድጋፍ እና በዲፕሎማሲ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ማገልገላቸውን ጠቅሷል።

ኢትዮጵያ ቼክ በጆርጅ ቦልተን የትዊተር አካውንት ላይ ባደረገው ማጣራት የፕሮፋይል ምስሉ (profile picture) የረቀቀ የማስመሰል ጥበብን (deep fake) በመጠቀም የተሰራ ሀሰተኛ ፎቶ መሆኑንን አረጋግጧል።

ይህ የረቀቀ የማስመሰል ጥበብን በመጠቀም thispersondoesnotexist.com በተባለ ድረ-ገፅ የተመረተ ሀሰተኛ የጆርጅ ቦልተን ምስል ከዚህ በፊትም የበርካታ ሀሰተኛ የትዊተር አካውንቶች እና ቦቶች ፕሮፋይል በመሆን አገልግሏል።

በዚህ ምስል ዙርያ ፋይናሺያል ፖስት ጥቅምት ወር ላይ ዜና ሰርቶ አጋርቷል: https://financialpost.com/technology/after-deepfakes-a-new-frontier-of-ai-trickery-fake-faces

የረቀቀ የማስመሰል ጥበብ በአርቴፊሻል ኢንቴሊጀንስ ቴክኖሎጂ በመታገዝ በነባራዊው ዓለም የሌሉ ሰዎችን ምስል የመስራት ክንውን ሲሆን ምስሎቹ ሀሠተኛ እና ቦት አካውንቶችን ለመክፈት በስፋት ጥቅም ላይ ይውላሉ።

ሌላው ኢትዮጵያ ቼክ ማረጋገጥ የቻለው በሁለቱ ትልልቅ ሚድያዎች በምንጭነት የተጠቀሰው የትዊተር አካውንት የተከፈተው ከስድስት ወራት በፊት ሲሆን እስካሁን በአካውንቱ ላይ የሚገኙ ፅሁፎች ስድስት ብቻ መሆናቸውን ነው።

የኢትዮጵያ ፕረስ ድርጅት እና ዋልታ ይህንን ዜና ካጋሩ በሗላ ትንሽ ቆይተው አጥፍተውታል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::