“መረጃው የተሳሳተ ነው። ፊፋ እስካሁን ይፋ ያደረገው ዝርዝር የለም፣ ለእኔም የደረሰኝ መረጃ የለም”— አልቢትር ባምላክ ተሰማ ለኢትዮጵያ ቼክ

“አልቢትር ባምላክ ተሰማ የአለም ዋንጫን እንደሚዳኝ ፊፋ አስታወቀ” እና “አልቢትር ባምላክ ተሰማ የአለም ዋንጫ ትኬቱን ቆርጧል” በሚል በስፋት የተሰራጨው መረጃ የሀሰት እንደሆነ አልቢትሩ ለኢትዮጵያ ቼክ አሳውቋል።

የመንግስት ሚድያዎችን ጨምሮ በርካታ የስፖርት ገፆች እና ግለሰቦች ጭምር ይህን ዜና በስፋት ተቀባብለውታል።

በነዚህ የተሳሳቱ መረጃዎች አባባል ፊፋ የኳታሩን የ2022 የዓለም ዋንጫ እንዲመሩ የመረጣቸውን ዳኞች ትናንት ይፋ አድርጎ ነበር፣ ለዚህም አፍሪካ ስምንት ዳኞችን ያስመረጠች ሲሆን ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ አንዱ ሆኖ ተመርጧል ይላል።

ኢትዮጵያ ቼክ አልቢትር ባምላክን በዚህ ዙርያ ያናገረ ሲሆን “መረጃው የተሳሳተ ነው። ፊፋ እስካሁን ይፋ ያደረገው ዝርዝር የለም፣ ለእኔም የደረሰኝ መረጃ የለም። እኔም ዜናውን ተፅፎ ያየሁት ሶሻል ሚድያ ላይ ነው” በማለት መልስ ሰጥቷል።

ወደፊት አለም ዋንጫውን ለመዳኘት የሚወጣ የዳኞች ዝርዝር ይኖር ይሆን ተብሎ የተጠየቀው አልቢትር ባምላክ ሲመልስ “ሊኖር ይችላል፣ ግን አሁን ማሳወቅ የምፈልገው እነዚህ አሁን የወጡት መረጃዎች የተሳሳቱ መሆናቸውን ነው” ብሏል።

የፊፋን ኦፊሴላዊ ድረ-ገፅ እና የማህበራዊ ሚድያ ገፆችንም የተመለከትን ሲሆን አለም ዋንጫን የሚዳኙ የዳኞች ዝርዝርን በተመለከተ እስካሁን ያወጣው መረጃ እንደሌለ ተመልክተናል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::