በኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር አካባቢ የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ እየወጡ ያሉ ሀሰተኛ መረጃዎች እና ምስሎች!

ይህ “አበበ ጎበዜ” የሚል የፌስቡክ ገፅ ከ7,800 በላይ ተከታይ ያለው ሲሆን በርካታ የተሳሳቱ እንዲሁም ያልተረጋገጡ መረጃዎችን ያጋራል፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ መረጃውን ወደ ሌሎች ያጋራሉ እንዲሁም አስተያየት ይሰጡበታል።

በትናንትናው እለትም በሰበር ዜና “የሱዳን ጦር ሰራዊት በምዕራብ ጎንደር 60 ኪሎ ሜትር ዘልቆ በመግባት አንድ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ አቃጠለ” የሚል መረጃ አጋርቷል። አክሎም “ይህ ሀይል ወደ መሀል ጎንደር እየገሰገሰ መሆኑ ተሰምቷል” ብሎ ፅፏል፣ ይህን ያስረዳል ያለውን እና ቃጠሎ የሚያሳይ ምስልም አያይዞ ለጥፏል።

ኢትዮጵያ ቼክ በምስሉ ላይ ባደረገው ማጣራት ከሁለት ቀን በፊት ባንግላዴሽ ውስጥ በሚገኝ አንድ የሮሂንግያ ስደተኞች መጠለያ ላይ የደረሰ ቃጠሎን የሚያሳይ እንደሆነ ተመልክቷል። በዚህም መሰረት ተያይዞ የቀረበው ምስል ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳልሆነ ታውቋል።

በሌላ በኩል “የሱዳን ጦር ወደ ኢትዮጵያ ጦር ዘልቆ ገብቶ ፋብሪካ አቃጠለ” በሚለው ዙርያም ማጣርያ አድርገናል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ጸጥታ ዘርፍ ሃላፊ አቶ እንዳላማው ማሩ “ፋብሪካ ተቃጥሏል፣ የሱዳን ጦር 60 ኪሎ ሜትር ዘልቆ ገብቷል የሚለው መረጃ ሀሰት ነው። ነገር ግን ሱዳኖች ትናንት እና ዛሬ ጠዋትን ጨምሮ በድንበር አካባቢ ጥቃት በመሰንዘር በአርሶ አደሮች ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ቀጥለዋል” ብለው ለኢትዮጵያ ቼክ ተናግረዋል።

ያልተረጋገጡ መረጃዎችን ባለማጋራት የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ይከላከሉ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::