በገንዘብ ሚኒስቴር ስም ተመሳስሎ የተከፈተ ሀሰተኛ የፌስቡክ ገፅ!

የገንዘብ ሚኒስቴር አርማን በመጠቀም እና ‘Ministry of the Finance- Ethiopia’ በሚል ስም የተከፈተ የፌስቡክ ገፅ ይገኛል። ገፁ የዛሬ ሳምንት የተከፈተ ሲሆን በተከፈተበት እለት ያጋራው አንድ ፅሁፍ ብቻ ከ7,000 በላይ መውደድ (Like) እና 91 መጋራት (Share) አግኝቷል።

ይህ በርካታ ግብረ-መልስ ያገኘው ፅሁፍ “ለ SMEs አስፈላጊ ማስታወቂያ” በሚል ይጀምርና “ከዩኤስኤአይዲ እና ከግሎባል ኢንተርፕረነርሺፕ ኔትዎርክ ጋር በመተባበር አነስተኛ ድርጅቶችን ከኢኮኖሚ ቀውስ እንዲያገግሙ የገንዘብ ድጎማዎችን በመስጠት ለመደገፍ ችለናል። በዚህ የገንዘብ ድጋፍ ፕሮግራም ውስጥ ለመካተት ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦች/ቢዝነሶች የበለጠ ለማወቅ እና የመስመር ላይ ማመልከቻዎችን እዚህ እንዲያቀርቡ ተጋብዘዋል” ብሎ አንድ የጉግል ቅፅ አያይዟል።

ኢትዮጵያ ቼክ የገንዘብ ሚኒስቴር ያለውን የተረጋገጠ (verification ምልክት ያለው) የፌስቡክ ገፅ የተመለከተ ሲሆን ይህ ከላይ የሰፈረው መልእክት እንደሌለ ተመልክቷል።

በተጨማሪም ከሚኒስቴር ዴታው አቶ ብሩክ ታዬ በሀሰተኛ አካውንቱ የቀረበው መረጃ የተሳሳተ እንደሆነ አረጋግጠናል። አቶ ብሩክ ሚኒስቴሩ እንዲህ አይነት ስራ ከዩኤስአይዲ ጋር እየሰራ እንዳልሆነ ጠቁመው “የተጠቀሙት ምስል የዛሬ አመት ገደማ ከፈረንሳይ ፓርላማ አባላት ጋር ውይይት ባረግንበት ወቅት የተወሰደ ነው” ብለዋል።

ትክክለኛው የገንዘብ ሚኒስቴር የፌስቡክ ገፅ: https://www.facebook.com/MoFEthiopia

ተመሳስለው የሚከፈቱ ገፆችን፣ አካውንቶችን እና ቻናሎችን ባለመከተል ራሳችንን ከሀሰተኛ መረጃ እና የጥላቻ ንግግሮች እንጠብቅ የሁልግዜ መልዕክታችን ነው።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::